Technology

ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን መግታት የሚያስችል ዲጂታል መመዝገቢያና መቆጣጠሪያ መተግበሪያ ተዘጋጀ >>የሠላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ መስከረም 27 / 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመግታት የሚያግዝ ዲጂታል የጦር መሣሪያ መመዝገቢያና መቆጣጠሪያ መተግበሪያ መዘጋጀቱን የሠላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአፍሪካ ደረጃ የሚከበረው ‘አፍሪካ አምነስቲ መንዝ’ የተሰኘው ከሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር የፀዳ ወር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከበረ ነው።

ይህንኑ በማስመልከትም የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅን የተመለከተ ጉባዔ ተካሂዷል።

በጉባዔው የጦር መሣሪያ መመዝገቢያና መቆጣጠሪያ መተግበሪያው በ2012 ዓ.ም የወጣውን ይህንኑ አዋጅ ለማስፈፀም እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።

የሠላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል “ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በአፍሪካ ሠላምና ደህንነት ላይ ግጭትና ስጋት በመፍጠር ሕዝቡን ለከፋ ጉዳት እየዳረገ ነው” ብለዋል።

በሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች ከቀላል እስከ ከፍተኛ የሽብር ጥቃት የዘለቁ ወንጀሎች እየተፈፀሙ ስለመሆኑም ገልፀዋል።

የአፍሪካ አገራት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ 2004 የፀደቀው የናይሮቢ ፕሮቶኮል መስራችና አባል ብትሆንም የጦር መሣሪያ ዝውውርና ቁጥጥር ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ እንዳልነበራትም ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት።

ይሁንና በ2010 ዓ.ም የተካሄደውን ለውጥ ተከትሎ በተሰራው ጠንካራሥራ የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ መውጣቱን ገልፀዋል።

“ኃይል መጠቀም የመንግስት ኃላፊነት ብቻ ነው” ያሉት ሚኒስትሯ “የሕግ የበላይነትን በማስከበርና አዋጁን ተፈጻሚ በማድረግ የኀብረተሰቡን ደህንነት እናረጋግጣለን” ብለዋል።

የሕዝቡን ሁለንተናዊ ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ጠቅሰው ለዚህ ስኬት ሕዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ፀረ-ሠላም ኃይሎችን መታገል እንዳለበት አሳስበዋል።

ለዚህም “በዘመናዊ መንገድ የተደገፈ የሕገ-ወጥ ጦር መሣሪያ ዝውውር ቁጥጥር ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉም ተናግረዋል ሚኒስትሯ።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በዜጎች ስነ-ምግባርና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ላይ መስራት እንደሚያሻም ጠቁመዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያን መቆጣጠር የሚያስችል በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ተዘርግቷል፤ በቅርቡም ምዝገባው ይጀመራል።

ለስራው የሚያስፈልገው የሰው ኃይል ስልጠናና ተቋማትን በቴክኖሎጂ የማደራጀት ስራዎች እየተሰሩ ሰለመሆኑ፤ አተገባበሩም ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እንደሚሆንም አክለዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው በበኩላቸው ኮሚሽኑ ከሠላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሥራዎችን ሲከውን መቆየቱን አንስተዋል።

በዚህም ለዘመናት ሥርዓት ሳይበጅለት የቆየውንና ቁጥጥርና አስተዳደሩ ደካማ የነበረውን የጦር መሣሪያ ዝውውር የተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ መደረጉን ተናግረዋል።

ይህን ስራ ለመምራትም ወቅቱ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ረገድ መተግበሪያው ስለሚኖረው ሚናም አስረድተዋል።