LatestNews

ጠ/ሚ ዐቢይ ለ1 ሺህ 495ኛው የነቢዩ መሐመድ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

 ኢትዮጵያችን የነቢዩ መሐመድን ልደት የሚያከብሩ ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች፣ ከነባር እምነት ተከታዮች እና ከሌሎችም ወገኖቻቸው ጋር ሆነው ለዘመናት በነጻነት ያቆዩዋት ሃገር ነች፡፡

ዛሬ ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር ሆነን የነቢዩ መሐመድን 1 ሺህ 495ኛውን ልደት ስናከብር የኢትዮጵያን ዳግም መወለድ እናስባለን፡፡

ስለ ህዝቦቿ ነጻነት እና ብልፅግና እንጨነቃለን፤ ኢትዮጵያ የእስልምና፣ የክርስትና እና የሌሎችም ነባር እምነቶች ሃገር በመሆኗ ህዝቦቿ በእምነቶቻቸው አይደራደሩም፤ በእድገታቸው አይደራደሩም፤ በነጻነታቸውም ቀልድ አያውቁም፤ እምነት ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወት ነው፡፡

ለዚህም ነው እምነታቸውን በፍጹም ልብ የሚወዱት፤ ለዚህ ነው በእምነታቸው የማይደራደሩት፤ ለዚህ ነው ታላቁን የመውሊድ በዓል በእንዲህ አይነት ድምቀት የሚያከብሩት፤ እንኳን ለ1 ሺህ 495ኛው ለታላቁ የመውሊድ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡

መውሊደል ነቢ፤ ራቢዩላዋል በተሰኘው ወር በ12ኛው ቀን በ570 አመተ ሂጅራ በመካ የተወለዱት የእስልምና ሃይማኖት መስራችና የአላህን ቁርዓን ለሰው ልጆች ያወጁት የታላቁ የእስልምና ነቢይ የልደት በዓል ነው ዛሬ፡፡

ይህን ታላቅ ቀን በቢሊየኖች የሚቆጠሩ የዓለም ሙስሊሞች፣ በሚሊየኖች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እና በወገኖቻቸው ሁሉ በድምቀት ይከበራል፡፡

በቅድመ ኮቪድ ጊዜ እንደነበረው ሰዎች ከሃገር ሃገር እየዞሩ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር በብዛት እየተሰባሰቡ ባይሆንም ቀኑ ታላቅና ልደቱም የነቢዩ መሐመድ ነውና በመስጊዶች፣ በመድረሳዎችና፣ መጅሊሶች በፍቅር እና በታላቅ ስሜት ይከበራል፤ የነቢዩ ልደት ስራ እና ህይወት ይዘከራል፡፡

ዛሬ ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር ሆነን የነቢዩ መሐመድን ልደት ስናከብር ሃገራችን ኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋ፣ ጎርፍ፣ ኮቪድ19 እና ሌሎችም ፈተናዎች እንደተደቀኑባት እያስታወስን ነው፡፡

ጉዟችን አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ወትሮም እናውቃለን፤ በየመንገዳችን ላይ እንቅፋት እንደሚኖር እንረዳለን ያም ሁሉ ሆኖ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች እና ሌሎችም እንደተለመደው እጅ ለእጅ ተያይዘን ፈተናዎቻችንን ሁሉ እንደምንሻገራቸው ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን እድል በኢትዮጵያውያን እጅ እንዳለ በፍጹም እናምናለን፡፡

ታላቁን የመውሊድ በዓል ስናከብር ምንጊዜም ልብ ልንለው የሚገባ ሌላም ቁምነገር አለ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን መውሊድን፣ ኢድን፣ ኢድ አልአድሃን በጋራ እና በፍቅር ለማክበር አዲስ እንዳልሆነው ሁሉ እንደ ሰሞኑ ያሉ ጊዜያዊ ችግሮችንም በጋራ ለማሸነፍ እና ወደ ፊት ለመራመድ አዲሶች አይደለንም፡፡

በሺህ ዘመናት አኩሪ ታሪካችን ውስጥ ረሀብንም፣ ቸነፈርን፣ ድርቅም ጎርፍም ደርሰውብን ሁሉንም አልፈን ነው እዚህ የደረስነው፡፡ ኢትዮጵያ ታሳልፋለች እንጂ አታልፍም፡፡

ነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) በመካ ተወልደው ሲያስተምሩ የተቀበሏቸው ጥቂት፣ የተቃወሟቸው ብዙ ነበሩ፡፡ ብዙዎች እየቆዩ ነው የተረዷቸው፡፡ ያመጡትን ለውጥ ለማስቀረት ብዙ ተደክሟል፡፡

በጽናት፣ በተጋድሎና በጊዜ ውስጥ ግን ብዙዎች ከጎናቸው ቆመዋል፡፡ የእኛም የለውጥ ጎዞ እንዲሁ ነው፡፡

በቆየው ኢትዮጵያውያን የመተባበር እና የመረዳዳት ባህል ታላቁን የመውሊድ በዓል ቤታችን ሆነን ስናከብር ቤት የሌላቸው ወይም በጎርፍም ሆነ በሌላ አደጋ ቤቶቻቸውን ያጡ ከሚኖሩበት ተፈናቅለው በየቦታው የተጠለሉ ወገኖቻችንን እናስታውስ፡፡

ስንበላ ስንጠጣ የሚበሉት የሚጠጡት የሌላቸው ያዘኑ የተቸገሩ ብዙዎች እንዳሉም አንርሳ፡፡

በልዩ ልዩ ምክንያት እንዲህ ለጊዜው የተቸገሩ ወንድም እህቶቻች እና ልጆቻችን በዓሉን አብረው እዲያከብሩ ያለንንነ እናካፍላቸው፡፡

የምንችለውን እናድርግላቸው ምንም ባይኖረን እንኳ ፍቅር እንስጣቸው፡፡

ፍቅር ከሁሉ ነገር ይበልጣል፡፡ መተሳሰብ እና መደጋገፍ ታላቅ ወንዝ ነው፡፡ ታላቅ ፈተናን ያሻግራል፡፡ ችግር የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡

በዓሉ ነገ ስለሚጠብቀን መልካም ጊዜ እያሰብን በፍቅርና በደስታ የምናከበረው በዓል ይሁንልን፤ ሁላችን ተሳስበን ከበሽታ ርቀን ጤንነታችንን ጠብቀን ሌሎችም እንዳይታመሙ አግዘን የምናከብረው ይሁን፡፡