ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት 6 ወራት 25.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ::

ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት 6 ወራት 25.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል። ገቢው ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀርም በ12 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል። ኢትዮ ቴሌኮም የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ሥራ አፈፃፀምን አስመልክቶ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬህይዎት ታምሩ መግለጫ ሰጥተዋል። ባለፉት 6 ወራት የኩባንያው የደንበኞች ብዛት 50.7 ሚሊዮን በላይ የደረሰ መሆኑንና አጠቃላይ የተመዘገበው የቴሌኮም አገልግሎት መሳሪያዎች ቁጥር 64 ሚሊዮን መድረሱንም ወ/ሪት ፍሬህይዎት ያብራሩት።ኩባንያው ለደንበኞች በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት በማቅረብ ረገድ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል። ኩባንያው 37 ምርትና የአገልግሎት ዓይነቶች ለገበያ ማቅረብ መቻሉም ተገልጿል። ኩባንያው 130 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እያከናወነ መሆኑም ተጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪም 322 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ ለማሕበራዊ ሀላፊነት ለመወጣት ድጋፍ ማድረጉንም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል። ኮቪድ 19፣ የሳይበር ጥቃትና የማጭበርበር ሙከራዎች እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የአገልግሎት መቋረጥ የበጀት ዓመቱ የ6 ወር ፈተናዎች እንደነበሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል።