በዳያስፖራው 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ወደ ሀገር ቤት መላኩ ተገለፀ::

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ማኔጅመንት የ2013 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸሙን ገምግሟል።በግምገማ መድረኩ ላይ የኤጀንሲው ያለፉት ስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ዝርዝር ሪፖርት በዕቅድና በጀት ክፍል ቀርቧል።በዚህም መሰረት ባለፉት ስድስት ወራት 821 የዳያስፖራ አባላት የውጭ ምንዛሪ አካውንት እንዲከፍቱ ድጋፍ መደረጉና ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ተቀማጭ መደረጉ፣ በዳያስፖራው 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ወደ ሃገር ቤት መላኩ እና ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ70 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡ ተጠቁሟል ለገበታ ለሃገር ከ20 ሚሊየን ብር በላይ፣ ለኮቪድ-19 መከላከያ በገንዘብና በአይነት ከ208 ሚሊየን ብር በላይ፣ ለሃገር መከላከያ ሰራዊትና ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ በገንዘብና በአይነት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡ ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ከ89 ቢሊየን ብር በላይ ላስመዘገቡ 847 የዳያስፖራ አባላት በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፎች እንዲሳተፉ ምልመላና ድጋፍ መሰጠቱ፣ የፋይናንስ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ 352 የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፎች እንዲሳተፉ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውም ነው የተገለፀው።በምህንድስና፣ በኮቪድ-19 መከላከል፣ በኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም በፐብሊክ ዲፕሎማሲና አድቮኬሲ ዳያስፖራው ዕውቀቱንና ክህሎቱን የሚያሸጋግርባቸው መድረኮች መመቻቸታቸው ሪፖርት መደረጉን ከኤጀንሲው ያገኘኘው መረጃ ያመለክታል። በሪፖርቱ 754 ዜጎች መብትና ጥቅማቸው እንዲከበር መደረጉን፣ 515 ዜጎች የህግ ድጋፍ ማግኘታቸውን፣ 6 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባባር ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ እንደተደረገ ተነስቷል።