የፕሮፌሰር ሂሩት ለአፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽነርነት የምረጡኝ ዘመቻ ተካሄደ::

የፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ለአፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽነርነት የምረጡኝ ዘመቻ መርሃግብር ተካሄደ።በመርሃግብሩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽን የአህጉሪቱ ነጻ የንግድ ቀጠና ትግበራን በቴክኖሎጂ በማገዝ በኩል ያለውን ቁልፍ ሚና አንስተዋል።ኢትዮጵያም ይህን ዕድል በመጠቀምና አህጉሩን ለማገልገል በትምህርት ዝግጁነት፣ በአመራር ችሎታና በስራ ልምድ የካበተ ልምድ ያላቸውን ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያምን ለዕጩነት አቅርባለች ነው ያሉት።ፕሮፌሰር ሂሩት በተመራማሪነት፣ በመሪነትና በሌሎች ያለፉባቸውና አሁን እያገለገሉባቸው የሚገኙ የሃላፊነት ቦታዎችን አቶ ደመቀ ዘርዝረዋል።በአመራር ጥበባቸው ለህብረቱ የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽን እሴት እንደሚጨምሩ እምነታቸውን ገልጸዋል።ለፕሮፌሰር ሂሩት ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮችና ሌሎች በመድረኩ የተገኙ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉም አቶ ደመቀ ጠይቀዋል።በመርሃ ግብሩ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ታዋቂ ሰዎችና ሌሎችም የክብር እንግዶች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።የኮሚሽኑ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ቢመረጡ በትምህርት ጥራትና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።