አሜሪካ 25 ሺህ ስደተኞችን ልትቀበል ነው

የጆ ባይደን አስተዳደር ሜክሲኮ የሚገኙ 25 ሺህ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ አሜሪካ እንዲገቡ እንደሚፈቅድ አስታወቀ።

ስደተኞቹ ወደ አሜሪካ መግባት ስላልቻሉ ሜክሲኮ በመሆን እየተጠባበቁ የነበሩ ሲሆን፣ በቀጣይ ሳምንት 25ሺህ ስደተኞች የኮቪድ-19 ምርመራ አድርገው ወደ አሜሪካ ይገባሉ ተብሏል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሰብዓዊ ደንብ የተከተለ እና ደህንነቱ የሚያስተማምን የስደተኞች ሥርዓት እንደሚዘረጉም ተገልጿል።

ስደተኞቹ ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት የሚያቀርቡበት ቀን እንደሚሰጣቸውና ከቤተሰቦቻቸውም ጋር የሚኖሩበት ቦታ እንደምቻች ተጠቁሟል።

ይህ ውሳኔ በሜክሲኮ የስደተኞች ማቆያ ሆነው ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚጠባበቁ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እጅግ አስደስቷል ሲል ቢቢሲ አስነብቧል።

እ.አ.አ በ2019 የወጣው የስደተኞች ፖሊሲ ጥገኝነት ጠያቂያዎች ጉዳያቸው በአሜሪካ እስኪታይ ሜክሲኮ እንዲቆዩ ያስገድዳል፤ ባይደን በመጀመሪያው የሥልጣን ቀናቸው ይህንን ፖሊሲ መሰረዛቸውም የሚታወስ ነው።