ሱዳን ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ቀረበልኝ ያለችውን ሽምግልና መቀበሏን አስታወቀች

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የገባችበትን የድንበርና የህዳሴ ግድብ ውዝግብ ለመፍታት ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ቀረበልኝ ያለችውን ሽምግልና መቀበሏን አስታወቀች፡፡የሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዳለው የሀገሪቱ ካቢኔ አረብ ኤምሬትስ አቀረበችው የተባለውን ከኢትዮጵያ ጋር የማሸማገል ዕቅድ ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡ በሌላ በኩል ግን የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትላንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የህዳሴው ግድብ ድርድር በሦስቱ ሀገራትና በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት ብቻ ነው ሊቋጭ የሚገባው ማለታቸው ይታወሳል፡፡ድርድሩ ወደ ሌላ ሦስተኛ ወገን ሊሄድ የሚችለውም በሦስቱ ተደራዳሪ ሀገራት ስምምነት ብቻ መሆኑን በቀደመው የሀገሪቱ መሪዎች የመርህ ስምምነት ወቅት በፊርማ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ድርድሩ በአንድ ሀገር የተናጠል ፍላጎት ወደ ሌሎች አደራዳሪዎች የሚካሄድበት ምክንያት እንደማይኖርና የሁለቱ ሀገራት ድንበርን በተመለከተም በሁለቱ ሀገራት ስምምነት የሚፈታ እንደሚሆን ጨምረው መናገራቸው ይታወሳል፡፡

#አዲስ_ነገር#Whatsnew_ebs