የኢቢኤስ አጫጭር የስፖርት መረጃዎች

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅቱን በአዳማ ከተማ እንደቀጠለ ነው። ልምምዱ ዋልያዎቹ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና እና ዚምቧቤ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ላሉባቸው ጨዋታዎች የታቀደ ነው፡፡ ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ በማቅረብ ዝግጅቱን የጀመረው የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስብስብም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስቴዲየም ዝግጅቱን መቀጠሉን ከእግርኳስ ፌደሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ ዋልያዎቹ ለዚህ ጨዋታ ይረዳቸው ዘንድም ከኡጋንዳ አቻቸው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ቀን መቁረጣቸውም ተሰምቷል፡፡

በአለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን የተሳተፉባቸው ውድድሮች ተካሂደዋል፡፡ በዚህም መሰረት በ1500 ሜትር ሴቶች ማጣሪያ ኢትዮጵያን የወከሉት ድርቤ ወልተጂና ሕይወት መሀሪ ተሳትፈዋል፡፡ በየምድባቸው ባደረጉት ውድድር አንደኛ እና ሁለተኛ የጨረሱት ድርቤና ሕይወት እሁድ ለሚደረገው ፍፃሜ ማለፍ ችለዋል፡፡ በሌላ በኩል በወንዶች የሶስት ሺህ ሜትር መሰናክል ማጣሪያ ሁለቱም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለፍፃሜው ያለፉበትን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ በማጣሪያው ላይ የተሳተፉት ሳሙኤል ፍሬውና ታደሰ ታከለ በየምድባቸው በተመሳሳይ ሁለተኛነት ደረጃ ውድድራቸውን ጨርሰዋል፡፡ ያንን ተከትሎም እሁድ በሚደረገው የፍፃሜ ውድድር የሚሳተፉ ይሆናል፡፡

የጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ቀጣዩን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የማስተናገድ አቅሙን በተመለከተ ግምገማ ተደርጎበታል። ስታዲየሙ ባሳለፍነው አመት የሊጉን የአምስት ሳምንታት መርሐ ግብሮች ማስተናገዱ ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ የቀጣዩን ዓመት ውድድር ለማስተናገድ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ግመገማ ተካሂዶበታል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርም ወደ ጅማ በማምራት የስታዲየሙን አሁናዊ ሁኔታ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የሀዋሳ ዩንቨርስቲ፣ አዳማ ዩኒቨርስቲ እና የድሬዳዋ ስታዲየሞች ግምገማ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

ማርቲን ኦዴጋርድ ወደአርሰናል የሚደርገውን ዝውውር አጠናቋል፡፡ ኖርዌያዊው የጨዋታ አቀጣጣይ ባሳለፍነው አመት በኢምሬትስ መልካም የሚባል የውሰት ጊዜን ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ በ 30 ሚሊየን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ ወደአርሰናል በቋሚነት የተመለሰ ሲሆን በሰሜን ለንደኑ ክለብ ስምንት ቁጥር መለያንም ተቀብሏል፡፡ የኦዴጋርድን መፈረም ተከትሎም አርሰናል በያዝነው ክረምት ያወጣው የዝውውር ሂሳብ ከ 100 ሚሊየን ፓውንድ በላይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ጄሲ ሊንጋርድ በማንችስተር ዩናይትድ ለመቆየት ማረጋገጫ እንደሚፈለግ ተነግሯል፡፡ እንግሊዛዊው የመስመር ተጫዋች በሳለፍነው አመት በውሰት ባመራበት ዌስትሀም አስደናቂ ጊዜ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ አሁን በኦልትራፎርድ የሚገኘው ሊንጋርድ ግን በዛው ለመቆየት በአዲሱ የውድድር ዘመን በቋሚነት እንደሚሰለፍ ከአሰልጣኝ ኦልጎነር ሶልሻየር ማረጋገጫ ይፈልጋል፡፡ ያንን ተከትሎም የዝውውር መስኮቱ ከመጠናቀቁ በፊት ከላንክሻየሩ ክለብ ሊለቅ የሚችልበት እድል እንዳለ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

ጋሪ ካሂል በይፋ በርንማውዝን ተቀላቅሏል፡፡ ከክሪስታል ፓላስ ጋር የነበረው የውል ስምምነት ተጠናቆ የነበረው የ 35 አመቱ የመሀል ተከላካይ በነፃ ዝውውር ጣፋጮቹን መቀላቀሉ ይፋ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የቼልሲ ተጫዋች በነገው ዕለት ከብላክ ቡል በሚኖረው ጨዋታ ለአዲሱ ክለቡ የመጀመሪያ ጨዋታውን ሊያደርግ እንደሚችል ተነግሯል፡፡ ጋሪ ካሂል በስታምፎርድ ብሪጅ ቆይታው የቻምዮንስ ሊግና ሁለት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

ካሪም ቤንዜማ በሪያል ማድሪድ ያለውን የውል ስምምነት አራዝሟል፡፡ ፈረንሳዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከሳንታያጎ በርናባው ከለቀቀበት 2018 አንስቶ አስደናቂ ጊዜን ሲያሳልፍ በሶስቱም የውድድር ዘመናት በእያንዳንዱ አመት ከ 20 በላይ ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ በመጨረሻም ለ ተጨማሪ አንድ አመት ውሉን በማራዘም እስከ 2023 በማድሪድ ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል፡፡ አዲሱ ውሉን ተከትሎም በማድሪድ ያለው የቤንዜማ ቆይታ 14 አመታትን የሚደፍን ይሆናል፡፡

ፓላንዳዊቷ አትሌት ማሪያ ማግዳኔላ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ሜዳሊዋን ለጨረታ ማቅረቧ ተሰምቷል፡፡ ማሪያ በጦር ውርወራ ያመጣችውን የኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ለጨረታ ለማቅረብ ያበቃትም የልብ ቀዶ ጥገና ለሚያስፈልገው የስምንት ወር ህፃን ህክምና ነው፡፡ በመጨረሻም የአትሌቷ ሜዳል ለመውሰድ ዛብካ የተሰኘ ድርጅት 125 ሺህ የአሜሪካን ዶላር አቅርቦ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ነገርግን ድርጅቱ ማሪያ ላሳየችው ከፍተኛ የበጎነት ተግባር ሜዳሊያው በአትሌቷ እጅ እንዲቆይ ወስኗል፡፡

ቻይና 109 ያህል ከኦሎምፒክ ጋር የተያያዙ የንግድ ስያሜ ጥያቄዎችን ውድቅ አድርጋለች፡፡ ለቻይና መንግስት ቀርበው ውድቅ የተደረጉት የንግድ ስያሜዎቹ በኦሎምፒኩ ለሀገሪቱ ውጤት ባመጡ አትሌቶች ስም የወጡ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የንግድ ስያሜዎቹ ከአትሌቶቹ በኩል ፍቃድም ሆነ እውቅና የላቸውም በሚል ውድቅ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ በኦሎምፒኩ በዳይቭ ወርቅ ያመጣችውን የ 14 አመቷን ኩዋን ሆንግቻንን ጨምሮ ብዙ የቻይና አትሌቶች ውድቅ በተደረጉት የንግድ መጠሪያዎች ላይ ስማቸው ተገኝቷል፡፡

ያሎትን አስተያየት እና ጥያቄ በአጭር መልዕክት 7696 ላይ ይላኩልን።

Join Our Telegram

Click Here To follow Us