የኢትዮጵያን ስም የያዙ የአቮካዶ ምርቶች ለአለም ገበያ በስፋት እየቀረቡ መሆኑን ተነገረ፡፡

የኢትዮጵያን ስም የያዙ የአቮካዶ ምርቶች ለአለም ገበያ በስፋት እየቀረቡ መሆኑን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ተናገረ። ኤጀንሲው በማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ለሶስት አመታት የያዘው ፕሮጀክት አንዱ አካል የሆነው አቮካዶን በብዛትና በጥራት የማምረት ሂደት በኦሮሚያ ክልል የሚገግኙ አርሶ አደሮችን በማማከር ምርታቸው በቆይታ ሳይበላሽ በጥንቃቄ ለአለም ገበያ ማቅረብ ተችሏል። ይህንኑ ተከትሎ ለመሆኑ ይህ ለ3 አመት የተዘጋጀ ፕሮጀክት እንዴት አቮካዶን ተመራጭ ሊያደርግ ቻለ ብሎ ኢቢኤስ አዲስ ነገር ጠይቋል።በምላሹም የውጪ ምንዛሬ ከማምጣት አንጻር፣በአለም ላይ ትልቅ ተፈላጊነት ያለው በመሆኑና በኢትዮጵያ የሚደርስበት ጊዜ ሌሎች አገሮች ላይ በማይበቅልበት ወቅት በመሆኑ እንደሆነ ሰምተናል። ከዚህም በተጨማሪ ለብዙ ሰው የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉ ተመራጭ እንዳደረገው የተናገረው ኤጀንሲው ከ53ሺ በላይ ዜጎችን በዘርፉ በማሳተፍ ላይ እንደሚገኝና እስካሁን ከ3ሺ 400 በላይ መሬት ማልማት መቻሉን አስታውቋል።በአማራ፣በደቡብ፣በኦሮሚያና ሲዳማ ክልሎች እየተተገበረ በሚገኘው ከዚህ ፕሮጀክት ከአማራ ክልል 1ሺ600 ኩንታል እንዲሁም ከኦሮሚያ 160 ኩንታል እስካሁን መገኘቱ ተጠቁሟል።