በአዲስ አበባ 10 ሺህ 500 የላዳ ታክሲዎች በአዳዲስ ታክሲዎች ሊተኩ ነው::

10 ሺህ 500 የላዳ ታክሲዎችን በአዳዲስ ለመተካት ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስአበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ::

10 ሺህ 500 ሰማያዊ በነጭ የላዳ ታክሲዎችን በአዳዲስ ታክሲዎች ለመተካት ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስአበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡ከሃምሳ ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጡትን እነዚህን ተሽከርካሪዎች በዘመናዊ ታክሲዎች መተካት የሚያስችል የስምምነት ፊርማ ስነስርዓት እየተካሄደ ነው።በሁነቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ስጦታው አካል ላዳ ታክሲዎች ከ10 ሺህ በላይ ቤተሰቦችን እንደሚያስተዳድሩ ገልጸው ታክሲዎቹ የበርካታ አዲስ አበባውያን ባለውለታ ናቸው ብለዋል፡፡አሁን ላይ ግን የከተማዋን እድገት የሚመጥን የትራስፖርት አገልግሎት ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንዲሁም የታክሲዎቹ ዕድሜና ይዞታ ዘመኑን የማይመጥን በመሆኑ ተሽከርካሪዎቹን በአዳዲስ መተካት ማስፈለጉን አስረድተዋል፡፡ ታክሲዎቹን በአዳዲስ ለመተካት ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ከንግድ ባንክ ብድር መመቻቸቱ የተገለፀ ሲሆን አዳዲሶቹ ታክሲዎች በሚቀጥሉት 4 ወራት ወደስራ እንደሚገቡ ይጠበቃል።