“በኮልፌና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች የተከሰተውን የእሳት ቃጠሎ መነሻ በማጣራት እርምጃ ይወሰዳል”

“በኮልፌና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች የተከሰተውን የእሳት ቃጠሎ መነሻ በማጣራት እርምጃ ይወሰዳል” ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ ::

በትናንትናው እለት በአዲስ ከተማ እና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች የተከሰተውን የእሳት ቃጠሎ መነሻ በማጣራት እርምጃ እንደሚወሠድና በቃጠሎው ለተጎዱ ነዋሪዎች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ።ምክትል ከንቲባዋ ዛሬ ጠዋት በኮልፌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 እፎይታ የገበያ ማዕከል በመገኘት በእሣት ቃጠሎ የደረሰውን ጉዳት ጎብኝተው የተጎዱ ነዋሪዎችን አጽናንተዋል።በሁለቱም አካባቢ የተነሣው እሣት ድንገተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በንብረታቸው ላይ ጉዳት የደረሠባቸው ነዋሪዎች መፅናናት እንዳለባቸው ገልፀው፤ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ከጎናቸው እንደሚቆም አረጋግጠዋል።“በአደጋው የተቃጠሉ የሱቆች እና የቤቶች ብዛት፣ በጠቅላላው የደረሰው ጉዳት በፖሊስ እየተጣራ ነው” ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤ የእሳት አደጋውን መነሻ ለማወቅ በሚደረገው ጥረት እና ለጋራ ሰላም ሲባል መረጃ ያለው ሰው ሁሉ ለህግ አስከባሪ እና ለፖሊስ መረጃውን በመስጠት እንዲተባበር ጠይቀዋል።መሰል አደጋ ዳግም እንዳይከሰት ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።ጉዳዩን በአፋጣኝ ለማጣራት ርብርብ እንዲደረግ ምክትል ከንቲባዋ ጥሪ ማቅረባቸውን የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪ አስታውቋል።