በየመን በእስር ቤት በደረሰው የእሳት አደጋ በርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው አልፏል

በየመን በደረሰው የእስር ቤት ቃጠሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው ማለፉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው እለት በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ፥ በአደጋው ህይወታቸው ያለፈ ኢትዮጵያውያን ትክክለኛ ቁጥር እየተጣራ ነው ብለዋል።

በኦማን መዲና ሙስካት የሚገኘው የኢትዬጵያ ኤምባሲም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።

ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር ከአደጋው የተረፉትን ከአካባቢው ለማስወጣት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ 733 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ነው አምባሳደሩ በመግለጫቸው ያነሱት።