ብልጽግና ፓርቲ የፓርቲውን ማኒፌስቶ እና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቱን ይፋ አደረገ
የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ የፓርቲውን ማኒፌስቶ እና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ይፋ አደረጉ::
“ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የምርጫ 2013 የብልጽግና ፓርቲ ማኒፌስቶ እና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ይፋዊ የእውቅና መድረክ በሸራተን አዲስ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የዕውቅና መድረኩን በእንኳን ደህና መጣችሁ የከፈቱት የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር አቶ ብናልፍ አንዷለም ፓርቲያችን ብልጽግና የአገራችንንና አለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በጥልቀት የገመገመ፣አገራችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በውል ለይቶ ትክክለኛ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ፣ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች በእኩል አካቶና አቅፎ የማታገያ ሜዳ ያመቻቸ፣በሚሊዬን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን በአባልነትና በደጋፊነት ከጎኑ ያሰለፈ፣በለውጥ ውስጥ የተወለደ፣ለለውጥ የሚተጋ፣የተስፋ ብርሐን የሰነቀ የዛሬና የነገ ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ ፓርቲው በምርጫ ወቅት የሚጠቀምበትን ማኒፌስቶና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክትን ይፋ አድርገዋል፡፡
በዚህም የፓርቲው መወዳደሪያ ምልክት እየበራ ያለ አምፖል ሆኗል፡፡
በመድረኩ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በርካታ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡