ትራምፕ በአፍሪካ ላይ ያራመዱትን ፖሊሲ እንደሚቀለብሱ የአሜሪካ የምክር ቤት አባል አስታወቁ

አዲሱ የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር ግሪጎሪ ሚክስ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በአፍሪካ ላይ ያራምዱት የነበረውን ፖሊሲ በአዲሱ አስተዳደር እንደሚቀለብሱ ገለጹ፡፡

የኮንግረስ አባሉ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ በሰብዓዊ እርዳታ እና በንግድ ጉዳዮች ዙሪያ ከሃገራቱ ጋር እንደሚሰሩ ነው የገለጹት፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በአፍሪካ የነበራቸው የዲፕሎማሲ ቡድን አነስተኛ እንደነበር የሚነገር ሲሆን የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊ ቦታም ለሁለት ዓመታት አምባሳደር ሳይሾምበት ቆይቶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

አሜሪካ ባለፉት ዓመታት ወደራቀችበት የዓለም መድረክ መመለሷን ገልጸው በድጋሚ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን ለማስተካከል ዕድል አግኝተናል ብለዋል፡፡

የቀድሞ የአሜሪካ አስተዳደር ፖሊሲ አፍሪካን የዘነጋ ሲሆን ትኩረቱን ቻይናና ሩሲያ ላይ አድርጎ እንደነበርም ነው ያብራሩት፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እስካሁን የጆ ባይደን አስተዳደር በአፍሪካ ላይ ያለው ዝርዝር አቋም ባይታወቅም አሜሪካ ወደ ዓለም አቀፍ ተቋማት መመለሷ በራሱ አፍሪካን ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ነው የፖለቲካ ተንታኞች የገለጹት፡፡

ምንጭ፡-አልጀዚራ