አዲስ ነገር – በሱዳን ካርቱም እና በተወሰኑ ከተሞች መረጋጋት እየሰፈነ ነው ተባለ፡፡
በሱዳን ለ7 ቀናት የሚዘልቀው የተኩስ አቁም ትግበራ እየተካሄደ መሆኑን ተከትሎ በመዲናዋ ካርቱም እና በተወሰኑ ከተሞች መረጋጋት እየሰፈነ ነው ተባለ፡፡
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሱዳን መዲና ካርቱም እና ሌሎች ከተሞች የአይን እማኞች ጊዜያዊ የተኩስ አቁሙ ገቢራዊ መደረግ መጀመሩን ተከትሎ “መጠነኛ እፎይታ እያገኘን ነው፤” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ በሱዳን የዳርፉር ግዛት የኤል ገኒና እና ኒያላ የተባሉ ከተሞች የሚኖሩ የአይን እማኞች ከአሶሺየትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ “የተሻለ መረጋጋት አግኝተናል፤” ብለዋል ።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የተደረሰው የተኩስ አቁምን በሚጥሱ ማንኛውም ተፈላሚ ኃይል ላይ አሜሪካ ማዕቀብ ልትጥል ትችላለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
🇷🇺#ሩሲያ
ሩሲያ ከዩክሬን ተነስተው ወደ ግዛቴ በመግባት ጥቃት የፈፀሙ የዩክሬን ሰርጎገብ ታጣቂዎችን ደምስሻለሁ አለች ።
የሩስያ – ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ከ 15 ወራት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዩክሬን ወደሩሲያ ድንበር ዘልቀው በመግባት ጥቃት የፈፀሙ 70 የዩክሬን ታጣቂዎችን መግደሏን ነው ሩሲያ ይፋ ያደረገችው ።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ሩሲያን ከዩክሬን በሚያዋስነው የቤልጐሮድ ግዛት በዩክሬን የተመለመሉ ታጣቂዎች የፈፀሙትን ጥቃት አክሽፈን አካባቢውን ወደ መረጋጋት መልሰናል ብሏል በመግለጫው፡፡
ዩክሬን በበኩሏ በሩሲያ የቀረበባትን ውንጀላ በማጣጣል ጥቃት አድራሾቹ የሩሲያ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ናቸው ስትል ምላሽ ሰጥታለች ተብሏል።
ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡
🇿🇦#ደቡብ አፍሪካ
የደቡብ አፍሪካው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጁሊየስ ማሌማ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ አደርጋለሁ ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል ።
የኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ የሆኑት ማሌማ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሩሲያ የደቡብ አፍሪካ ሁነኛ ወዳጅ ሀገር በመሆኗ እና የምትፋለመው ኢምፕሪሊስቶችን ስለሆነ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ አደርጋለሁ ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ ከዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንድትወጣ ፓርቲያቸው ፍላጎት እንዳለውም ነው ማሌማ ያስታወቁት፡፡
ማሌማ ፍርድ ቤቱ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በሚቀጥለው ወር በሚካሄደው የብሪክስ ጉባኤ ላይ ለመታደም በሚመጡት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ያወጣው የእስር ማዘዣን ተቃውመዋል።
🇯🇵#ጃፓን
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ሀገራቸው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት በምህጻረ ቃሉ ኔቶ አባል መሆን እንደማትፈልግ አስታወቁ ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ኔቶ በእስያ የመጀመሪያው የሆነውን ድጋፍ ሰጪ ጽህፈት ቤት ሊከፍት እቅድ መያዙን አስመልክቶ መረጃው እንዳላቸው ባስታወቁበት ጊዜ ነው ።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ኔቶ በጃፓን ሊከፍት ነው የተባለውን ድጋፍ ሰጪ ጽህፈት ቤት አስመልክቶ ቻይና ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተለች መሆኗን አስታውቋል፡፡
ዘገባው የሬውተርስ ነው።
ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ
👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30
👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)
👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00
ዘወትር ቅዳሜ
👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት
ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ዜናዎች በፍጥነት እና በየእለቱ ይዘገቡበታል።
አዲስ ነገር / What’s New