ኢትዮጵያ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኤምባሲዋን እንደገና ለመክፈት ማቀዷን ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ገለጹ::

የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኤምባሲዋን በቅርቡ እንደገና  ለመክፈት ማቀዷን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቷ ይህንን ያስታወቁት  ከሀገሪቱ  ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺሴኬዲ ጋር በኪንሻሳ ብሄራዊ ቤተመንግስት ከተወያዩ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አያይዘውም የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ የአፍሪካ ህብረት የሊቀመንበርነት ስፍራን ለሚረከቡት የዲሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ተልእኳቸው የተሳካ እንዲሆን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል፡፡

ሁለቱ ፕሬዚዳንቶችም በኪንሻሳ እና በአዲስ አበባ መካከል ያለውን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከመወያየታቸውም ባለፈ  በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳቦችን ተለዋውጠዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሳህለ-ወርቅ የታንዛኒያ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መጓዛቸው ይታወሳል።