ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 830 ፋብሪካዎችን ዳግም ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።
በንቅናቄው 4 ነጥብ 85 ቢሊየን ዶላር ገቢ ምርትን በመተካት እና 433 ሚሊየን ዶላር ከወጪ ንግድ በማስገኘት የተሳካ የኢንዱስትሪ ሽግግር ውጤት ማስመዝገቡንም ነው ተቋሙ የገለፀው።
ይህ ሽግግር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተወዳዳሪነት ከጥሬ ዕቃ ላኪነት ወደ ቴክኖሎጂ ላኪነትና ክህሎት አቅራቢነት ከፍ የሚያደርግ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ መሠረት የሚጥል መሆኑን ነው አገልግሎቱ ያስታወቀው።
ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ክፍያ በሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ብቻ ይተዳደሩ የነበሩ ውስብስብ የቴክኖሎጂ ሲስተሞች፣ ዘመናዊ የምርት መስመሮችና የሶፍትዌር መሠረተ-ልማቶች ዛሬ ላይ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ወጣት መሐንዲሶችና ቴክኒሻኖች እየተመሩ እንደሚገኙም ተመልክቷል።
ይህም ከኢኮኖሚያዊ ስሌቶች ባሻገር ኢትዮጵያን የዕውቀትና የክህሎት ምንጭ በሚያደርገው የሰው ሀብት ልማት ላይ ትልቅ ስትራቴጂካዊ ስኬት የተመዘገበ መሆኑን አመላካች ነው ተብሏል።
ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ
