News

ኤምባሲው የውትድርና ምልመላ ጥያቄዎችን እንደማይቀበል አስታውቋል

በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ ምላሽ

ኤምባሲው ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ኢትዮጵያዊያን በአካል እና በኢሜይል በሚልኳቸው መልዕክቶች ለሩሲያ ያላቸውን ድጋፍ እና አጋርነት እየገለጹ መሆናቸውን በመጠቆም ይህ በሁለቱ አገራት መካከል የማይሰበር ወንድማዊ ወዳጅነትን እንደሚገልጽ አስታውቋል፡፡

በዚህ አጋጣሚ እየታዩ ያሉ የአጋርነት ጥያቄዎችን ብሎም የኢትዮጵያ መንግስት ከዩክሬን ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ጨምሮ ሌሎች ሩሲያን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙርያ በተመድ ያሳየውን ድጋፍ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ያደነቀው ኤምባሲው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያደረገች ያለችውን ጦርነት የአገሪቱ ጦር በብቃት እንደሚወጣው ያለውን እምነት ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ኤምባሲው የውትድርና ምልመላ በሌላ አገር ማድረግ ተቀባይነት የለውም የሚለውን የ1961 የቪየናን ኮንቬሽን ስምምነት እንደሚያከብርና በዚህ መሠረትም ምንም አይነት የምልመላ ጥያቄዎችን እንደማይቀበል አመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የዩክሬን ኤምባሲ ከሩሲያ ኤምባሲ ቀደም ብሎ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ሩስያውያን ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ለመመልመል ሲሞክሩ እየታየ ነው ነገር ግን  እውነታውን ለመግለጽ አልፈለጉም ሲል በማህበራዊ የትስስር ገጹ አስነብቧል፡፡ እንዲሁም ሰሞኑን በርካታ ወጣቶች የተለያዩ ሰነዶችን ይዘው በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ በር ላይ ተሰልፈው መታየታቸው የሚታወስ ነው፡፡