ኮሪያ ሆስፒታል በየቀኑ ለ200 ድሃ ዜጎች ህክምና የሚሰጥ ማዕከል ሊገነባ ነው
ኮሪያ ሆስፒታል በመባል የሚታወቀው የምዩንግሰንግ ህክምና ማዕከል ሁለት የህክምና ማዕከላት ሊያስገነባ መሆኑን አስታወቀ።
ከሚገነቡት ህንጻዎች አንደኛው አጋፔ ቪዥን ማዕከል የሚሰኝ ሲሆን በዚህ ማዕከል ውስጥም የልብ ህክምና፣ የጨጓራና አንጀት ህክምና፣ የነርቭ እንዲሁም የካንሰር ህክምና የሚሰጥበት ማዕከል እንደሚደረግም ሆስፒታሉ ለጣቢያችን በላከው መግለጫ አስታውቋል።
እንዲሁም ሌላኛው “የቅድመ መከላከል ማዕከል” የሚሰኘውና በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት ይሰጣል የተባለው የህክምና ማዕከል በቀን እስከ 200 ሰዎች ድረስ የሚያስተናግድ እንደሚሆንም ተገልጿል።
ኮሪያ ሆስፒታል በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር 2004 የተቋቋመ ሲሆን በስሩ የተከፈተው የምዩንግሰንግ ህክምና ኮሌጅ በኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያዎችን ከ2012 ጀምሮ እያሰለጠነ እንደሚገኝ ተቋሙ በመግለጫው አስታውቆናል፡፡ ሪፖርተራችን ሳሚ በላይ እንዳጠናቀረው፡፡