የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት 10ኛ ዓመት መከበር ጀምሯል።

የህዳሴ ግድብ 10ኛ ዓመትን በማስመልከት በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ አስተባባሪነት በግድቡ ድርድር ላይ የተሳተፉ እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን እንዲሁም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተገኙበት ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው፡፡ሲምፖዚየሙን በንግግር የከፈቱት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን ዓባይን ማልማትና የህዳሴ ግድቡን ማጠናቀቅ ለነገው ትውልድ ከመስራት በላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ጭምር ነው ብለዋል፡፡ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ዶ/ር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ አጠቃላይ ግንባታ 79% እንደደረሰ ገልፀዋል፡፡በቀጣዩ ክረምት ቀጠሮ የተያዘለት 2ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማይራዘምና ለዚያ የሚያበቃ አሰራርና ምክንያትም እንደሌለ ዶ/ር ስለሺ ተናግረዋል፡፡ሲምፖዚየሙ የግድቡን አጠቃላይ ሁኔታ እንዲሁም የሶስትዮሽ ድርድሩ የደረሰበትን ደረጃ ለመግለጥ እና ግብዓት ለመሰብሰብ ብሎም የግድቡን 10ኛ ዓመት ለመዘከር የተዘጋጀ ነው፡፡