የዓለም የጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት ብቻ በመላው ዓለም ከሁለት መቶ ሰባት ሺህ በላይ ሕፃናት በኩፍኝ በሽታ ለህልፈት መዳረጋቸውን አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ ከአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ተቋም ጋር በጋራ ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው በአውሮፓዊያኑ በ2019 ብቻ በመላው ዓለም 8 መቶ 70 ሺ ያህል ሕፃናት በኩፍኝ በሽታ ተይዘዋል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በ26 ሀገራት ከ94 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ሕፃናት የኩፍኝ ክትባቶችን ለማዳረስ የተጀመረውን ጥረት የኮሮና ወረርሽኝ አስተጓጉሏል ማለታቸውን አሶሲየትድ ፕሬስ በዘገባው አመልክቷል፡፡
የኩፍኝ ክትባቶችን 95 በመቶ ለሚሆኑ ሕፃናት ማዳረስ የሚያስፈልግ ቢሆንም አሁን ያለው ስርጭት 70 ከመቶ ብቻ መሆኑ አሳሳቢ ነው ሲሉ የድርጅቱ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡
በኩፍኝ በሽታ የሚሞቱ በርካቶቹ ሕፃናት በታዳጊ ሀገራት እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡