ዲኤስቲቪ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭትና የውድድር ስያሜ በ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ገዛ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ኩባንያ የፕሪሚየር ሊግ ውድድሩን በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ለማስተላለፍ ፍላጎት ያላቸውን ድርጅቶች ባወጣው ጨረታ መሠረት ሲያወዳድር ቆይቷል።

ከተወዳዳሪዎቹ መካከልም የደቡብ አፍሪካው ኩባንያ መልቲቾይዝ ባቀረበው የቴክኒክና የፋይናንስ ትልመ ሀሳብ /ፕሮፖዛል/ የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ በቀጣይ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን ኩባንያው በሚያስተዳድረው ዲኤስቲቪ አማካኝነት እንዲያስተላልፍ መመረጡን ከኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ኩባንያው ውድድሩን በቀጥታ ለማስተላለፍና ለውድድር ስያሜ ለአምስት ዓመት 22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር አቅርቧል።

በተጨማሪም መልቲቾይዝ ለስልጠናና አቅም ግንባታ፣ ለፕሮዳክሽን፣ ለአየር ሠዓት ወጪና ለኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ግንባታ ከ45 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ያደርጋል ተብሏል።

በአጠቃላይ ኩባንያው በአምስት ዓመት ውስጥ ከ68 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ወጪ እንደሚያደርግ መግለጹንና በዚሁ መሰረት የስርጭትና የውድድር ስያሜ መብት አሸናፊ መሆኑ ተመልክቷል።

ኩባንያው የኢትዮጵያን የስፖርት ደረጃ ለማሻሻል በታዳጊ ወጣቶች፣ በዳኞችና አሰልጣኞች አቅም ግንባታ፣ በስታዲየም አካባቢ ጸጥታና ሌሎች ጉዳዮች ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ተጠቅሷል።

ኩባንያው በቅርብ ቀናት ውስጥ ከሊጉ አክሲዮን ኩባንያ ጋር የውል ስምምነት በማድረግ ወደ ስራ እንደሚገባ ማስታወቁን ከስፖርት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የደቡብ አፍሪካው ኩባንያ መልቲቾይዝ እ.አ.አ በ1995 የተቋቋመ ሲሆን ዲኤስቲቪን ጨምሮ ሌሎች የሳተላይት ቴሌቪዥንና የበይነ መረብ የተንቀሳቃሽ ምስል አማራጮችን በስሩ የያዘ ነው።

ትኩረቱን ከሰሀራ በታች በሚገኙ አገራት ያደረገው ኩባንያው በ50 የአፍሪካ አገራት 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ደንበኞች እንዳሉት መረጃዎች ያሳያሉ።