ግብጽ ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሀ ሙሌት የናይል የውሀ አቅርቦቴን አያስተጓጉልም ስትል በድጋሚ አረጋግጣለች፡፡

ግብጽ ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሀ ሙሌት የናይል የውሀ አቅርቦቴን አያስተጓጉልም ስትል በድጋሚ አረጋግጣለች፡፡ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የግብጹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሽኩሪን ጠቅሶ እንደዘገበው በቅርቡ የሚካሄደው የህዳሴ ግድብ የውሀ ሙሌት የግብጻዊያን የውሀ ፍላጎትን የሚጎዳ አይደለም፡፡ በአስዋን ግድብ በቂ ውሀ አጠራቅመናል ያሉት ሳሚህ ሽኩሪ በዚህ ረገድ ግብጻዊያን ምንም አይነት የውሀ ደህንነት ስጋት ሊገባቸው አይገባም ብለዋል፡፡ ሁለተኛው ዙር የውሀ ሙሌት የሚፈጥረው ጫና ባይኖርም እኛ ያለንን የውሀ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ያለችግር ልንንቀሳቀስ እንችላለን ሲሉም አክለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡ ሳሚህ ሽኩሪ ይህን ያሉት በተለይ በሱዳን ጉዳይ ላይ በሚያተኩረው የፓሪስ አፍሪካ ጉባኤ ወቅት ከሀገራቸው ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት በዚህ መድረክም ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ተገኝተው እንደነበር ተመልክቷል፡፡ ሽኩሪ ኢትዮጵያ የግድቡን ውሀ መጠቀም ያለባት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ብቻ መሆን አለበት ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ግብጽና ሱዳን በቀደመው አቋማቸው ሁለተኛው ዙር የውሀ ሙሌት ከመካሄዱ በፊት ከኢትዮጵያ ጋር አስገዳጅ ስምምነት እንፈርም ይሉ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ከግብጽ ወገን የአቋም ለውጥ ታይቷል፡፡።