ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ 1442ኛውን የኢድ አል-ፊጥር በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል

ክፉውን ጊዜ እንደ ዒድ ሶላት ሰብሰብ ብለን ልንጋፈጠው፣ በኅብረታችን የሚገጥሙንን ፈተናዎች እንደ ምንሻገራቸው ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያን እድል በእኛው እንጂ በሌላ በማንም እጅ እንዳልሆነ ለዓለም ማሳየት ይኖርብናል ሲሉ መልክታቸውን ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ዛሬ የእንኳን አደረሳቹ መልእክት ባስተላለፉበት ጹሁፋቸው ሲሆን የዘንድሮውን ዒድ አል ፈጥር የምናከብረው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በርካታ ፈተናዎች እንደተደቀኑባት እያስታወስን ነው ብለዋል፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ለግላችን ሳይሆን ለጋራ ህልውናችን እንድናስብ የሚያስገድደን፣ ከግል ምቾታችን በላይ ለጋራ ደኅንነታችን እንድንተጋ በእጅጉ ግድ የሚልበት ጊዜ መሆንንም በመጠቆም በሕዳሴ ግድብ እና ከፊታችን ባለው ምርጫ ምክንያት ሀገራችን ፈተናዎቿ ቢበዙም ሀገራችን ለዘመናት የተቆለሉባትን ችግሮች ፈቀቅ በማድረግ ከሌሎች ጥገኝነት ነጻ እንደሚያደርገን፣ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያለንን ተቀባይነት በማሳደግ በኩል ሁለቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶቻችን ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡“ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ” እንደሚባለው፣ በሕዳሴ ግድብና በሌሎች ሀገራዊ ጥቅሞቻችን ላይ እንደ ችሎታችን የበኩላችንን ብንታገል ለዘመናት የሀገራችን ችግሮች ፈውስ የሚሆን አቅም መፍጠር እንችላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እያንዳንዳችን የተለያየ የፖለቲካ እምነት ሊኖረን ቢችልም ያለችን ግን አንድ ሀገር ፣ ህዝብ መሆንን መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡ በዒድ አል ፈጥር በዓል ዋዜማ ላይ ሆነን ስለ ምሕረት፣ ስለ ይቅርታ እና ስለ ፍቅር እንጂ፣ ስለ ጠብና ጥላቻ ማሰብ እንደሚያስቸግር በመግለጽም ቀጣይ ጊዜያትም ስለ አንድነት እንጂ፣ ስለ መለያየት የምንዘምርባቸው ጊዜያት እንደማይሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል። በተቀደሰው የረመዳኑ ወር ለሀገራችሁ ጸጋና በረከት፣ ሰላምና ፍቅር እንደ ጾማችሁና እንደ ጸለያችሁ ሁሉ፥ በክብረ በዓሉም፣ ከዚያ ወዲያ ባሉት ቀናትም ለሀገራችንና ለሕዝባችን ዱዐ ማድረጋችሁን እንድትቀጥሉ ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።