በበዓል ግብይት ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶች ሊሰራጩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ እንዲደረግ ተጠየቀ
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበአል ግብይት ወቅት ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶች ሊሰራጩ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳሰበ።
ኮምሽኑ ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ በገበያና በሌሎች ሥፍራዎች ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ዝግጅት ማድረጉንም አስታወቋል።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ በተለይ የሕዝብ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው የገበያ ማዕከላትና በመዝናኛ ሥፍራዎች ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ ክትትል እንዲሁም ጥበቃ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በበዓላት ግብይት ወቅት ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች በገበያው ሊሰራጩ እንደሚችሉ የጠቆሙት ኮማንደሩ ኅብረተሰቡ እንዳይታለልና አጠራጣሪ የብር ኖቶችን ሲመለከትም ለፖሊስ ጥቆማ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል። የባንኮችን ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መጠቀም እንዲህ ያሉ ወንጀሎችን ለመከላከል አስተዋጾ እንዳላቸው የጠቀሱት ኮማንደር ፋሲካ ኅብረተሰቡ ማንኛውንም አጠራጣሪ የወንጀል ድርጊቶችን ሲመለከት በአካል ወይም 991 ነጻ የስልክ ጥሪ በመጠቀም መጠቆም እንደሚችል አመላክተዋል።