ሱዳን የውስጥ ጥያቄዋን በድንበር ችግሮች ለመሸፈን እየሞከረች ነው
የኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይ ላይ ከሱዳን በኩል እየተሰነዘሩ ያሉ ሀሳቦች ውስጣዊ ችግርን በውጪያዊ ጉዳይ ለማስረሳት የሚደረጉ ጥረቶች ናቸው ብሏል።
ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ይህን ያለው በዛሬው እለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም ቢሆን ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ጉዳይ መፍታት የሚፈልገው በሰላማዊ መንገድ መሆኑንም ገልጿል።
በዚሁ መግለጫ ላይ የአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም ወደ ትግራይ የሚላከው የሰብአዊ ድጋፍ ከሚፈለገው ያነሰ ነው በማለት በትዊተር ገፃቸው ላይ ያሰፈሩትን መረጃ በተመለከተ የተጠየቀው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የችግሩ ምንጭ መንግስት አይደለም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
አለም አቀፉ ማህበረሰብም እርዳታው በተፈለገው መጠን እንዳይዳረስ ምክንያት የሆነው ማን እንደሆነ ማጣራት ይገባዋል ያለው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በህወሃት በኩል ያሉ ትንኮሳዎች የሚቀሩ ከሆነ በመንግስት በኩል ድጋፉ እንዲደርስ እገዛ እንደማይጓደል ጠቁሟል።
በትላንትናው እለት የሩሲያ ኤምባሲን አቋም በመደገፍ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ስለወጣው መግለጫ የተጠየቁት ቃልአቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በግላችን ምንም የማጣራት ስራ ባንሰራም ኤምባሲው ኢትዮጵያዊያንን ለጦርነት አልመለመልኩም ሲል ያወጣውን መግለጫ በበጎ መልኩ ተቀብለነዋል ብለዋል።