በሙስና ያገኘው ነው የተባለ ከ22.7 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግስት ተወርሷል
ከዚህ በፊት በሙስና ወንጀል በ11 ዓመት ፅኑ እስራትና በ65 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወስኖበት የነበረው ግለሰብ በወንጀሉ ያገኘው ከ22 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግስት እንዲወረስ ተደርጓል፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳመለከተው ግለሰቡ ከታህሳስ 2006 እስከ ታህሳስ 2008 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ነው በአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በመሳለሚያ߹ ካዛንችስና አራዳ ቅርንጫፍ ከሚሰሩ ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር የሙስና ወንጀሉን የፈጸመው፡፡
በዚህም በአንድ የመኪና ሊብሬ በተለያዩ የተቋሙ ቅርንጫፎች ብድር በመውሰድ߹ በአንድ የመኪና ታርጋ በተለያዩ ግለሰቦች ስም ለዋስትና በማስያዝና ብድር በመወስድ ብሎም ለብድር በቂ ስንቅ የሌለው ቼክ በማቅረብ የሙስና ወንጀል መፈጸሙ ተመልክቷል፡፡
በመሆኑም በወንጀሉ ያገኘው ወደ 23 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ህጋዊ ወለዱን ጨምሮ ከሀብቱ ላይ ተሰብስቦ ለመንግስት ገቢ ሆኗል የተባለ ሲሆን በሙስና ተግባሩ ተሳትፎ የነበራቸው የተቋሙ ሰራተኞችም በወንጀል እንዲጠየቁ መደረጉን አስታውቋል፡፡