News

ሰራተኞች ኑሮ እየከበዳቸው በመሆኑ መንግስት መፍትሔ ማበጀት አለበት አለ-ኢሰማኮ

በኢትዮጵያ የሚገኙ ሰራተኞች በአሁኑ ሰአት እየተከፈላቸው ባለው ዝቅተኛ ደሞዝ የተነሳ የኑሮን ጫና መቋቋም የማይችሉበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው መንግስት የሰራተኞች ኑሮ እንዲሻሻል ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ተናግሯል፡፡

ኢሰማኮ ለጣቢያችን በላከው ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ በተለይም በከተሞች ያለው የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ካደረጉ ነገሮች መካከል የመኖሪያ ቤት እጥረት አንደኛው በመሆኑ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በፍጥነት ተጠናቀው ለዜጎች የሚተላለፉበት ሂደት ሊፈጠር ይገባል ብሏል፡፡

በተጨማሪም ኮንፌዴሬሽኑ የሰራተኞች ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል በሀገሪቱ ተግባራዊ እንዲደረግና ደንቡም እንዲጸድቅ የጠየቀ ሲሆን አቅም ያላቸው የውጭ ሃገራት ባለሀብቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና በሀገር ውስጥ ያሉ ባለሀብቶችም ያለው የጸጥታ ስጋት ተቀርፎ በተገቢው መንገድ መስራት እንዲችሉ መንግስትን ጠይቋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የሰራተኞች የመደራጀትና የመደራደር መብትን በፈረመቻቸው የአለም ስራ ድርጅት ስምምነቶች በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ የተረጋገጠ ይሁን እንጂ አሁንም አንዳንድ አሰሪዎች ሰራተኞቻቸውን መደራጀት እየከለከሉ መሆኑን ጠቁሞ አሰሪዎችና የአዋጁ አስፈጻሚ አካላት የሰራተኞችን የመደራጀትና የመደራደር መብት ሊያከብሩ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተቋሙ ከሰራተኞች ጉዳይ ወጣ ብሎም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ለመንግስት ምክሩን የለገሰ ሲሆን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የተገመተውን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ብሎም አካታችና ተአማኒነት ያለው እንዲሆን፤ መንግስት በጉዳዩ ላይ ጥያቄ አለን የሚሉ ወገኖችን ሁሉ በማዳመጥ መፍትሄ ማፈላለግ ይኖርበታል ሲል በላከው የአቋም መግለጫ አመላክቷል፡፡ ሪፖርተራችን ማዕዶት አየለ እንዳጠናቀረችው፡፡