ኢትዮ ቴሌኮም አሻም ቴሌና ቴሌ ገበያ የተሰኙ አገልግሎቶችን አስተዋውቋል
ኢትዮ ቴሌኮም በነጥብ አሰጣጥ ላይ የተመሰረተ ሽልማት የሚሰጥበትን አሰራር ለደንበኞቹ ይፋ አድርጓል።
አሻም ቴሌ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ አዲስ የነጥብ ሽልማት ደንበኞቹ በታማኝነት አብረው ለመዝለቃቸው የሚበረከት ስጦታ ነው ያለው ኢትዮ ቴሌኮም የድምፅ የፅሁፍ መልእክት ብሎም የኢንተርኔት አገልግሎትንና ቴሌ ብርን የሚጠቀሙ ደንበኞቹ ይህን ሽልማት ያገኛሉ ብሏል።
የነጥብ ሽልማቱን ለማግኘት ደንበኞች በማይ ኢትዮ ቴሌ መተግበሪያ እንዲሁም በ999 ቴሌ ገበታ በኩል መመዝገብ እንደሚገባቸውና የተመዘገቡ ደንበኞች ማንኛውንም የ1 ብር የቴሌኮም አገልግሎት ሲጠቀሙ 1 ነጥብ፣ በቴሌ ብር የ10 ብር ግብይት የሚፈፅሙም እንዲሁ 1 ነጥብና በቴሌ ብር ካርድ የሚሞሉ ደግሞ 2 ነጥብ እንደሚያዝላቸው ተነግሯል።
1 ነጥብ የ0 ነጥብ ዜሮ ሁለት ሳንቲም ዋጋ ይኖረዋል ያለው ኢትዮ ቴሌኮም ደንኞች ባጠራቀሙት የነጥብ ገንዘብ የተለያዩ ጥቅሎችን መግዛትና የአገልግሎት ክፍያ መፈፀምን ጨምሮ ጠርቀም ካለም ከተቋሙ ሞባይልና ሌሎች መገልገያዎችን ሊገዙበት እነደሚችሉ አሳውቋል።
ከዚህ በተጨማሪ ቴሌ ገበያ የተሰኘና በኦንላየን የስልክ ቀፎን ጨምሮ ሌሎች የቴሌኮም ግብዓቶች የሚሸጡበትን ድረገፅ ያስተዋወቀ ሲሆን ከቴሌ ገበያ ዶት ኢትዮቴሌኮም ዶት ኢቲ ላይ የሚሸምቱ ሰዎች በቴሌ ብር ከከፈሉ በኋላ እቃዎቻቸውን በያሉበት አደርሳለሁ ብሏል። የአቤል አበበ ዘገባ ነው፡፡