የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሲቲያን የአደባባይ በዓላትን የሚከታተልና ቁጥጥር የሚያደርግ መምሪያ እንዲደራጅ ሃሳብ ቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሲቲያን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስር የአደባባይ በዓላትን የሚከታተልና ቁጥጥር የሚያደርግ መምሪያ እንዲደራጅ ሃሳብ ቀረበ፡፡ይህ ሃሳብ የቀረበው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀኖናና ዶግማ መሰረት በአደባባይ የሚከበሩት እንደ መስቀልና ጥምቀት ያሉት በዓላት ያጋጠሟቸውን ስኬትና ተግዳሮቶች የሚዳስስ የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡በውይይት መድረኩ እኚህ የአደባባይ በዓላት ለሃይማኖቱ ተከታዮች ከሚሰጡት መንፈሳዊ ጥቅም ባሻገር ለሃገር የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ለምጣኔ ሃብቱ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ነው ተብሏል:: በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዘጋጅነት በተካሄደው ውይይት ላይ ለአደባባይ በዓላቱ ፈተናና መፍትሄ ናቸው የተባሉ ነጥቦችም ተነስተዋል፡፡