መንግስት ለትግራይ 100 ቢሊዮን ብር ለሰብዓዊ ድጋፍና ለሌሎች ስራዎች ማውጣቱን አሳወቀ፡፡

መንግስት በትግራይ ክልል አካሄድኩ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ የመከላከያ ሰራዊቱን ወጪ ሳይጨምር 100 ቢሊዮን ብር ለሰብዓዊ ድጋፍና ለሌሎች ስራዎች ማውጣቱን አሳውቋል፡፡ መንግስት ይህን ያሳወቀው ከክልሉ መከላከያ ሰራዊቱን ያስወጣበትን ወታደራዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ለመገናኛ ብዙሃን በገለጸበት ጊዜ ነው፡፡ መግለጫውን የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንና ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ ሲሆኑ የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔው ለትግራይ ህዝብ በማሰብ የተወሰነ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ውሳኔው አሸባሪ የተባለው ህውሃት ከፊት ለፊት ወጥቶ ከመዋጋት ይልቅ ህዝብን በዘር በመቀስቀስ ከፊት በማስቀደም ንጹሃንን ለችግር ለመዳረግ ያለውን ጥረት ለማክሸፍም ያሰበ ነውም ተብሏል፡፡ ወትሮም ቢሆን ወደ ክልሉ የገባነው ህግ ለማስከበር እንጂ እንደ መቀሌና ሌሎች ከተሞች ያሉ አካባቢዎችን ነጻ ለማውጣት አይደለም ያሉት ሌተናል ጀነራል ባጫ አሁን ከመቀሌ ወጥተን ሌሎች አካባቢዎችን ብንይዝ ልዩነት የለውም ነው ያሉት፡፡ጨምረውም መቀሌ ጦርነቱን ስንጀምር የስህበት ማእከል በመሆኗ ዋነኛ መዳረሻችን የነበረች ብትሆንም አሁን ግን ያን አቅሟን በማጣቷ ከመጥቀም ይልቅ ሸክም ሆናብናለች ነው ያሉት፡፡