የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት ከአከራይና ተከራይ ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች ትናንት ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።
ኃላፊዋ በየዓመቱ የሚደረገው የቤት ኪራይ ዋጋ ማሻሻያ ጥናት ፍጹም በህጋዊው ውል ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው ከህግ ውጪ የሚደረጉ ማናቸውም የጎንዮሽ ውሎች ተቀባይነት አይኖራቸውም ብለዋል፡፡
በመሆኑም ህግ ጥሰው በሚገኙ አካላት ላይ የተጀመረው ህጋዊ እርምጃና ተጠያቂነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊዋ አሳስበዋል።
አዲሱ የቤት ኪራይ መጠን የተወሰነው በዘፈቀደ እንዳልሆነ የገለፁት ኃላፊዋ የህዝብ ብዛትን፣ የዜጎችን የመክፈል አቅምና ያለውን የቤት አቅርቦት መሰረት ባደረገ ሳይንሳዊ ጥናት መሆኑን አብራርተዋል።
ኃላፊዋ አከራዮች በዘፈቀደ ዋጋ መጫን የማይችሉበት እንዲሁም ደላሎች ተከራዮችን በየጊዜው እያቀያየሩ በመሃል የሚያተርፉበት ያልተገባ አሠራር መቀረፉን ገልፀዋል።
በሁሉም ክፍለ ከተሞች የአከራይ ተከራይ ውል እድሳት እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።
