በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሳምንቱ የተጠናቀቁ ዝውውሮች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሳምንቱ የተጠናቀቁ ዝውውሮች
ኢትዮጵያ ቡና
በዝውውር መስኮቱ በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙት ቡናማዎቹ አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን በይፋ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድርገው የሾሙ ሲሆን ባልተጠበቀ መልኩ በክልል ክለቦች ሻምፒዮና በሻኪሶ ከተማ ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳዩትን አንተነህ ተፈራ፤ብርሃኑ ወልቂጦን እና የኛነህ ታሪኩን ወደ ቡድናቸው ቀላቅላዋል፡፡ ከእነሱ በተጨማሪም ያለፈውን አመት በሰበታ ያሳለፈውን አማኑኤል ወልደዩሃንስ እና የሃዋሳውን አማካይ ሄኖክ ድልቢን የግላቸው አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ መድኅን
አዲስ አዳጊዎቹ በበኩላቸው የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የሆኑትን አብድልከሪም መሃመድ፤ ጸጋሰው ድማሙን እና ተካልኝ ደጀኔን ወደ ቡድናቸው አምጥተዋል፡፡
ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ባለፈው አመት በሰበታ ከተማ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየውን ግብ ጠባቂ ሰለሞን ደምሴ የመጀመሪያ ፈራሚው ያደረገው ሌላኛው አዲስ አዳጊ ክለብ በሳምንቱ የታፈሰ ሰርካን እና የሙሴ ካቤላን ዝውውርም አጠናቋል፡፡ ግብጠባቂው ዘሪሁን ታደለ፤ተከላካዩ አብነት ደምሴ እንዲሁም አጥቂዎቹ ኢብራሂም ከድር እና ስንታየሁ ዋልጬ ደግሞ ውላቸውን አድሰዋል፡፡
ሲዳማ ቡና
ሌላው በሳምንቱ በዝውውር መስኮቱ በንቃት ሲሳተፍ የቆየው ሲዳማ ቡና የቀድሞ ተጫዋቾቹን አንተነህ ተስፋዬን እና አበባየሁ ዩሃንስን ወደ ቡድኑ ሲመልስ የአርባ ምንጩን አጥቂ ጸጋዬ አበራን እና ኢኳቶሪያል ጊኒያዊውን የቀድሞውን የመቀሌ ግብ ጠባቂ ፍሊፕ ኦቮኖን ዝውውር አጠናቋል፡፡
ባህርዳር ከነማ
ባለፈው የውድድር አመት ከፍተኛ የመወረድ ስጋት ተጋርጦባቸው የነበሩት የጣና ሞገዶቹ በበኩላቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ውሉን እንዳራዘመ ሲነገር የቆየውን አማካይ ያብስራ ተስፋዬን ፤በአዲስ አበባ በግሉ ጥሩ ጊዜ ያሳለፈውን እና ለሲዳማ ቡና ለመፈረም ተስማምቶ የነበረውን ናይጄሪያዊው የተከላካይ አማካይ ቻርለስ ሪባኑ እንዲሁም የግራ መስመር ተከላካዮቹን ተስፋዬ ታምራትን እና ፍራኦል መንግስቱን የግላቸው አድርገዋል፡፡
ድሬዳዋ ከተማ
ዮርዳኖስ አባይን ዋና አሰልጣኛቸው አድርገው በመሾም ወደ ዝውውር መሰኮቱ የገቡት ቡርትካናማዎቹ እየተገባደደ ባለው በዚህ ሳምንት የአራት ተጫዋቾችን ፊርማ አግኝተዋል፡፡የአዳማው አማካይ ዮሴፍ ዩሃንስ፤ ያለፈውን አመት በአዲስ አበባ ያሳለፉት አጥቂው ቢኒያም ጌታቸው እና የቀኝ መስመር ተከላካዩ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ እንዲሁም የቡራዩ ከተማው አጥቂ ጫላ በንቲ ለክለቡ ፊርማቸውን ያኖሩት ተጫዋቾች ናቸው፡፡
ወልቂጤ ከተማ
አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን ጨምሮ በርካታ ተጨዋቾቻቸውን የተነጠቁት ሰራተኞቹም የባህርዳር ከነማዎቹን አፈወረቅ ሃይሉን እና ሳለአምላክ ተገኝን አስፈርመዋል፡፡
ወላይታ ዲቻ
በሳምንቱ የግራ መስመር ተከላካዩን ሳሙኤል ተስፋዬን በማስፈረም ወደ ዝውውር ገበያው የገቡት የጦና ንቦቹ ያለፈውን አመት በወልቂጤ ያሳለፈውን አማካይ በሃይሉ ተሻገር(አኪራ) ወደ ቡድናቸው ሲቀላቅሉ የአምበላቸውን ደጉ ደበበ እና የአማካዩን ነጋቱ ገብረስላሴን ውል አራዝመዋል፡፡
መከላከያ
በዝውውር መስኮቱ በርካታ ትልልቅ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ያመጣው ጦሩ በዚህ ሳምንትም የፋሲሉን የግራ መሰመር ተከላካይ አምሳሉ ጥላሁን(ሳኛ) እና በሃድያ ሆሳና ውሉን ለማራዘም ተስማምቶ የነበረውን ተስፋዬ አለባቸው(ቆቦ) የግላቸው አድርገዋል፡፡
ሃድያ ሆሳና
በዝውውር መስኮቱ እምብዛም ተሳትፎ እያደረጉ የማይገኙት ነብሮቹ ተከላካዩን ዳግም ንጉሴን እና ሁለገቡን ተጫዋች ቤዛ መድኅንን ማስፈረማቸው ተረጋግጧል፡፡
ፋሲል ከነማ
አጼዎቹ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የተለያየውን አማካይ ታፈሰ ሰለሞንን ሲያስፈርሙ የግብ ጠባቂያቸውን ሚኬል ሳማኪ ውል አድሰዋል፡፡
አርባ ምንጭ ከተማ
አዞዎቹ ደግሞ ያለፈውን አመት በቤንች ማጂ ቡና ያሳለፈውን አጥቂ ወንድማገኝ ኬራን ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል፡፡
ሪፖርተር፡ ነቢል መሐምድ