Sports

ኢትዮጵያ በ18ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና

በኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ እየተመራ ወደ 18ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያቀናው የኢትዮጵያ ልዑክ ውጤታማ ጊዜ ያሳለፈበትና ኢትዮጵያዊነት ነግሶ የታየበት የአለም ሻምፒዮና ሆኖ አልፏል፡፡

በሴቶች 10,ሺ ሜትር በለተሰንበት ግደይ ድል የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያን በማሳካት ውድድሩን በጥሩ መንፈስ የጀመረው የኢትዮጵያ ልዑክ ከዚያም በመቀጠል በወንዶች ማራቶን በአትሌት ታምራት ቶላ ፣በሴቶች ማራቶን በአትሌት ጎትይቶም ገ/ስላሴ እና በ ሴቶች 5,000 ሜትር በጉዳፍ ጸጋዬ አማካኝነት በአጠቃላይ 4 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሳካት በኢትዮጵያ የአለም ሻምፒዮና ታሪክ በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎች የተመዘገቡበት የአለም ሻምፒዮናም ለመሆን በቃ፡፡ ቡድኑ በውድድሩ ከ 4 የወርቅ ሜዳሊያዎች በተጨማሪም 4 የብር እና 2 የነሃስ ሜዳሊያዎችንም ማሳካት ችሏል፡፡

በውድድሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ከአለም ሁለተኛ ከአፍሪካ ደግሞ 1ኛ ሆኖ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ቡድን በውድድሩ ደምቆ ከመታየቱም በላይ በምንግዜም የአለም ሻምፒዮና የደረጃ ሰንጠረዥ 1 ደረጃን አሻሽሎ 6ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥም ችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በሄልሲንኪ አለም ሻምፒዮና ከፍተኛ የነበረውን 9 ሜዳሊያ ማስመዝገቧ የሚታወስ ሲሆን የዘንድሮው የአለም ሻምፒዮና ግን በርካታ ሜዳሊያዎች የተመዘገቡበትና ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት የአለም ሻምፒዮና ነው፡፡

በተለይም በአለም ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ እምብዛም በማትታውቅባቸው የ1,500 ሜትርና መሰናክል ውድድሮች ሜዳሊያን ማስመዝገብ የቻለች ሲሆን ይህም በአጭር ርቀት ውድድር ላይ በደንብ ከተሰራ ውጤት ማምጣት እንደሚቻልም ያሳየ ሆኗል

ኢትዮጵያ ካገኘቻቸው 10 ሜዳሊያዎች 7ቱ የተገኙት በሴቶች ሲሆን ኢትዮጵያ በምትታወቅበትና ብዙ ሜዳሊያዎችን በምታሳከበት የ 5 እና 10 ሺ ሜትር ወንዶች አንድም ሜዳሊያ አለመመዝገቡ አግራሞትን ፈጥሮ አልፏል፡፡

ሪፖርተ፡ ሳምራዊት ሀብቴ

የኢቢኤስ የአዲስ ነገር / What’s New መረጃዎችን በሚከተሉት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ይከታተሉ::

ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ

👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)

👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00

ዘወትር ቅዳሜ

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት

አዲስ ነገር / What’s New

EBSTV WRLDWIDE

EBSTV WRLDWIDE

EBS