በጦርነቱ ሳቢያ የ12ኛ ክፍል ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች ድጋሚ ይፈተናሉ ተባለ
በጦርነትና በግጭት ውስጥ ሆነው የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱና የማለፊያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች ከዘንድሮው የመደበኛ ተፈታኝ ተማሪዎች ጋር እኩል ድጋሚ ይፈተናሉ ሲል ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በጦርነትና በግጭት መካከል ሆነው የ2013 ዓ.ም የመልቀቂያ ፈተና የወሰዱና የማለፊያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች በዚህ ዓመት በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተናን እንደ መደበኛ ተማሪዎች መፈተን እንደሚችሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዛሬ ለተመረጡ የመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።
ትምህርት ሚኒስቴር በመግለጫው አክሎም የፈተና ውጤት ማሳወቅን በተመለከተም በሁለት ዙር ፈተና ከመሰጠቱ ጋር ተያይዞ አጋጥሞ የነበረው ችግር መታረሙና ከዩኒቨርስቲዎች ጋር ውይይት በማድረግ ተጨማሪ የቅበላ አቅም እንዲኖርና ይህም በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ክልሎች በፍትሀዊነት እንዲከፋፋል ውሳኔ ላይ መደረሱን በማህበራዊ የትስስር ገጹ አስፍሯል።
በተመሳሳይ ከዚሁ ከ12ኛ ክፍል ፈተና ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ያዋቀረው ኮሚቴ ባደረገው ምርመራ የደረሰበትን በቅርቡ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ የክልል ትምህርት በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሳወቀው በ2013 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ወስደው ወደ ዩኒቨርስቲ የመግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎችን አስመልክቶ ሁለት ውሳኔዎች በትምህርት ሚኒስቴር መወሰናቸውን ገልጿል።
የመጀመሪያው ውሳኔ ከዚህ በፊት በተላለፈው የመቁረጫ ነጥብ መሰረት ወደ መንግሥት ዩኒቨርስቲዎች መግባት ከቻሉት የክልሉ ተማሪዎች በተጨማሪ 4 ሺህ 339 ተማሪዎች በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ቅበላ እንዲያገኙ ተውስኗል ሲል አስታውቋል፡፡
እንዲሁም የክልሉ ትምህርት ቢሮ እንዳለው ከሆነ ሁለተኛው ውሳኔ ደግሞ የክልሉ የሁሉም ዞኖች ተማሪዎች በ2014 ዓ.ም በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በመደበኛ ተማሪነት መፈተን እንዲችሉ ተወስኗል ብሏል፡፡