News

ለቅዱስ ላልይበላ ገዳም ስምንት ሚሊዮን ብር ተሰበሰበ::

የቅዱስ ላልይበላ ገዳም ካህናትና አገልጋዮችን ለመደገፍ በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ስምንት ሚሊዮን ብር ያህል መስበሰቡ ተሰምቷል፡፡

“ወደ ቅዱስ ላልይበላ ተመልክቱ!” በሚል መሪ ቃል  በሸራተን አዲስ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ትናንት የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡

በመርኃግበሩ ላይ የሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን (ከሚሴ) አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በአካባቢው ባለፉት አሥር ወራት የመብራት አገልግሎት ከመቋረጡ ጋር ተያይዞ የውሃ፣ የህክምና፣ የወፍጮና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን  አመልክተዋል።

እንዲሁም ደብሩ በተለያዩ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ካህናት፣ የቅርሱ ጠባቂዎችና ነዋሪዎች ያለውን ጥሪት ቆጥቦና ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ተበድሮ ህዝቡን ለመመገብ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንም  አያይዘው ገልጸዋል ።

በገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት  የባህል ሚኒስትር ዲኤታ  ስለሺ ግርማ በበኩላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ወደ አከባቢው እንዲሄዱ ሰፊ ጥረት ቢደረግም በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነት ትልቅ ጫና ከመፍጠሩ ባሻገር በተለይ በቅርሱ ዙሪያ ባሉ ነዋሪዎች ሕይወት ላይ ትልቅ ፈተና ሆኗል ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ ከተለያዩ ወገኖች  ስምንት ሚሊዮን ብር ያህል የተሰበሰበ ሲሆን ስጦታው ጅምር በመሆኑ በመላው ዓለም የሚገኙ ወገኖች አሁንም ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ ተላልፏል።