የልጃገረዶች ክብረ በዓል
ልዩ ልዩ መጠሪያ ስሞች ያሉት በአብዛኛው ሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በተለየ ሁኔታ በአካባቢው በሚገኙ ልጃገረዶች የሚከበረው በዓል ነው፡፡
#በትግራይ “አሸንዳ”
#በዋግ ኽምራ “ ሻደይ”
#በላስታ “አሸንድዬ”
#በቆቦ አካባቢ “ሶለል”
#በአክሱም አካባቢ ደግሞ “ዓይነ ዋሪ” እየተባለ ሲጠራ ሰሞኑን መከበር ጀምሯል።
ይህ በዓል በክረምት ወቅት ከሚበቅለው አሸንዳ ከተባለ ለምለም ተክል ስሙን እንደወረሰ ይነገራል። ሴቶችና ልጃገረዶችም የዚህን ተክል ቅጠል በወገባቸው አሸርጠው በቡድን በቡድን በመሆን ይጨፍራሉ፣ ሽልማት ይቀበላሉ ሽልማት ያልሰጣቸውን ደግሞ በግጥሞቻቸው በመሸንቆጥ ያከብሩታል።
የአሸንዳ በዓል የፀጉር አሠራሩ፣ ከአልባሶ እሰከ ግልብጭ፣ ከጋመ እስከ ድርብ፣ ከደቃቅ እስከ ጉልህ፣ ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ከቱባው ባህል ልብስ አንስቶ እስከ ዘመናዊው ስፌት፣ አቀናጅተው ለብሰውና ተውበው በልጃገረዶች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ትልቅ በዓል ነው።
ጌጣጌጡም ልዮ ነው፤ አንገት ላይ ከሚንጠለጠለው ሕንቆ፣ እግር ላይ እስከሚጠልቀው አልቦ የልጃገረዶቹን ውበት አይን አዋጅ ያደርገዋል። ታዲያ ይሄን ውበት የተመለከቱ አባቶችም ያሸንዳ ልጅ አይተህ ሚስት አትጭ የሚል ተረት አላቸው ምክንያቱም ደሞ ሁሉም ቆንጆ ሆነው አምረው እና ደምቀው ነው የሚታዩት ይላሉ።
መልካም በዓል!
ዘገባው የዮሀንስ አበረ ነው።