የአንበጣ ወረርሽኝ በደረሱ ሰብሎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ለኅብረተሰቡ ጥሪ ቀረበ

የአንበጣ ወረርሽኝ ስርጭት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ በደረሱ ሰብሎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ኅብረተሰቡ የመከላከል ዘመቻው አካል እንዲሆን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርና ሚኒስቴር የአንበጣ ወረርሽኝ መከላከል ቴክኒክ ቡድን ጋር በጽህፈት ቤታቸው ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ የቴክኒክ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት የአንበጣ ወረርሽኝ ስርጭት ፈጣን እና ሰፊ መሆኑ የመከላከል ሥራውን እጅግ ፈታኝ ማድረጉን ገልጿል።

የመከላከል ሥራው ኬሚካል በሚረጩ አውሮፕላኖች መታገዝ ስላለበት ከጐረቤት ሀገራት ለአንበጣ ማጥፊያ የሚያገለግሉ አውሮፕላኖችን በድጋፍ ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆኑንም የኮሚቴው አባላት ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ በበኩላቸው፣ የአንበጣ ወረርሽኝ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ እና ለመከላከል የተጀመሩ ጥረቶች መጠናከር እንዳላባቸው አሳስበዋል።

የአንበጣ ወረርሽኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እና በስፋት መጨመሩ በደረሱ ሰብሎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አሳሳቢ መሆኑንም አንሥተዋል።

መንግሥት ችግሩን ለመከላከል የጀመረው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኅብረተሰቡም የመከላከል ዘመቻው አካል እንዲሆን ጥሪ ማቅረባቸውን ከጽ/ቤታቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።