የአፍሪካ ህብረት የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተናጠል እመረምራለሁ ማለቱን የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሟል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በትግራይ ተፈፀመ የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተናጠል እመረምራለሁ ማለቱን የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሟል፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ህብረቱ በተናጠል ምርመራ አደርጋለሁ ማለቱ ሕጋዊ መሰረት የለውም ሲል ተቃውሞውን አቅርቧል፡፡ከዚህ ቀደም በመሪዎች ደረጃ በተካሄደው የህብረቱ የፀጥታና ሰላም ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር በትግራይ ተፈፀመ የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመመርመር ፈቃደኝነቷን ገልፃ እንደነበር መግለጫው አስታውሷል፡፡ ይህን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር ምርመራው ለማከናወን መስማማቱን ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር በፃፈው ደብዳቤ ማረጋገጡንም መግለጫው ጠቅሷል፡፡ ይሁንና የሁለቱ ወገኖች ስምምነት ሳይኖር ኮሚሽኑ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ በተናጠል ምርመራውን አካሂዳለሁ ማለቱ እንግዳ ነገር እንደሆነበት የኢትዮጵያ መንግሥት በመግለጫው አመልክቷል፡፡ ኮሚሽኑ እንደ ህብረቱ ተቋምነቱ ከአባል ሀገራት ጋር ተባብሮና በገንቢው ሚና ተጫዋችነት ሊሰራ ይገባል የተባለ ሲሆን በዚህም አሁን ኮሚሽኑ ጀመርኩት ያለውን ምርመራ በአስቸኳይ አቋርጦ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ተቋማት ጋር በመነጋገር ኃላፊነቱን እንዲወጣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግጫው አሳስቧል፡፡