የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት
የፌዴራል መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ከ2 ነጥብ 339 ትሪሊየን ብር በላይ ሆኖ መቅረቡ ተገልጿል።
የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 25ኛ መደበኛ ስብሰባው የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ የፌዴራል መንግሥት የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን በተመለከተ ባቀረቡት የበጀት መግለጫ ላይ ተወያይቷል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ የ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት የረቂቅ በጀቱን መግለጫ ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት በጀቱ መንግሥት የያዛቸውን የልማትና የማክሮ ኢኮኖሚ ዕቅዶች ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ለ2019 በጀት ዓመት ከቀረበው በጀት ውስጥ 1 ነጥብ 236 ትሪሊየን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 568 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለካፒታል ወጪ እንደሚውል አስረድተዋል።
በተጨማሪም 520 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለክልሎች የበጀት ድጋፍ እንዲሁም 14 ቢሊየን ብር ለክልሎች የዘላቂ ልማት ግብ ማስፈጸሚያ ይውላል ነው ያሉት።
ከአጠቃላይ በጀቱ ውስጥ 52 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆነው በጀት ለመደበኛ ወጪ የተመደበ መሆኑን ገልጸው ከዚህም ውስጥ 542 ቢሊየን ብር ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ የእዳ ክፍያ እንደሚውል ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ከዚሁ የመደበኛ ወጪ ውስጥ 236 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለማዳበሪያ፣ ለነዳጅ ድጎማ እንዲሁም የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅትን ካፒታል ለማሳደግ የተመደበ ሲሆን ለመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ለደመወዝ፣ ለአበልና ልዩ ልዩ ክፍያዎች ደግሞ 170 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር መመደቡን ገልጸዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2019 በጀት ዓመት 10 ነጥብ 1 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃልም ብለዋል።
#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
