ያልተሳካው የሰላም ድርድር
በፌደራል መንግሥት እና ሸኔ ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል በታንዛንያ ዳሬ ሰላም ሲደረግ የነበረው ድርድር ያለውጤት መጠናቀቁን መንግስት አስታውቋል። የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ጽ/ቤት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ከሸኔ ጋር በሁለት ዙር ሲካሄድ የቆየው ንግግር ያለውጤት ተጠናቋል ያለ ሲሆን ከወራት በፊት በዚያው በታንዛኒያ ዛንዚባር በተካሄደው ንግግር ቡድኑ ከ60 ዓመታት በፊት የኦሮሞም የሌሎች ብሔርብሔረሰቦች የነበሩ እና ተመልሰው ያደሩ ጥያቄዎችን አንስቷል ብሏል ። በወቅቱ ቡድኑ ከለውጥ በኋላ ስራ ላይ የዋሉ ጉዳዮችን ከመደጋገም ውጭ የሚቆጠር አጀንዳ ማምጣት ባለመቻሉ ሂደቱ ተንጠልጥሎ እንዲቆይ ማድረግ ተመራጭ ነበር ብሏል።ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዳሬሰላም በተደረገው ንግግርም ቡድኑ የድርድር ነጥቦቹን አገሪቱ ከደረሰችበት ሁኔታ አንጻር ለማጣጣም ይሞክራል የሚል ተስፋ እንደነበር ጠቅሷል። ይሁንና ቡድኑ መንግስት አዝሎ መንግስት ያድርገኝ ከማል አጉራ ዘለልነት ሲል የጠቀሰውን አቋም ከማንጸባረቅ ያለፈ የድርድር ነጥብ ማምጣት አልቻለም ብሏል። የፌዴራል መንግስት ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ከግማሽ መንገድ በላይ ተጉዞ ሙከራ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን ቡድኑ ግን በሰላም ጊዜ እንዴት መኖር እንዳለበት ማሰብ ቸግሮት ታይቷል ብሏል። የፌዴራል መንግስትን ልዑክ በመምራት በንግግሩ ላይ የተሳተፉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልእክት መንግስት ሰላም እንዲሰፍን በመሻት በድርድር ይዘትም ሆነ ሂደት በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ያለው የመፍትሔ አማራጭ ለማቅረብ ስለመሞከሩ አንስተዋል ። ይሁንና በሌላኛው ወገን አቋሙን ለመቀየር ግትርነት በማሳየቱ ድርድሩ ያለስምምነት ሊጠናቀቅ እንደቻለ ገልጸዋል።አምባሳደር ሬድዋን አክለውም ድርድሩ በዋናነት ያለስኬት ሊጠናቀቅ የቻለው በቡድኑ የአደናቃፊነት አካሄድና ባቀረባቸው እውነታነት የሌላቸው ጥያቄዎች መሆኑን ገልጸዋል ። በነገራችን ላይ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነመንግስታት አደራዳሪነትና በአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ታዛቢነት በታንዛንያ በተካሄደው በመጀመሪያው ዙር ድርድር ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራውና መንግስት በሽብርተኝነት የፈረጀው ቡድን በውጭ በሚኖሩ ተወካዮቹ አማካኝነት የተሳተፈ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ግን በአደራዳሪዎች እገዛ በልዩ በረራ ወደስፍራው በተጓዙት ዋና አዛዡን ኩምሳ ድሪባ ወይም ጃል መሮን ጨምሮ በወታደራዊ አዛዦቹ አማካኝነት በቀጥታ ተሳትፍ አድርጓል።ከፌደራል መንግስት በኩል በመጀመሪያው ዙር የልዑኩ አባል ከነበሩት የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተጨማሪ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የመረጃ ዋና መምሪያ ሃላፊ ጀነራል ጌታቸው ጉዲና ተሳትፈዋል። መንግስት ሸኔ የሚለውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድንም ባወጣው መግለጫ ድርድሩ ያለውጤት መጠናቀቁን የገለጸ ሲሆን የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ ለመመለስ መንገድ ለመክፈት ያስችላሉ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ላይ ለውጥ ያመጣሉ ያላቸውን አካታች ምክረሃሳቦች በድርድሩ ላይ አቅርቦ እንደነበር ገልጿል።ይሁንና የፌዴራል መንግስት የአገሪቱን መሰረታዊ የፖለቲካ እና የጸጥታ ችግሮች መፍታት ከመጀመር ይልቅ የሰራዊቱን አመራር በከፊል የመቆጣጠር ፍላጎት አሳይቷል ሲል ከሷል።
ዜናውን የኤርሚያስ በጋሻው ነው።