News

አዲስ ነገር – አጫጭር የዓለም መረጃዎች

🇸🇩#ሱዳን
የሱዳን ጦር ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ከልዩ ኃይሉ ጋር ሲያካሂድ ከነበረው ውይይት ራሱን ማግለሉን አስታወቀ፡፡
የሱዳን ጦር በአሸማጋይ ሀገራት አማካይነት ከሚካሄደው የተኩስ አቁም ውይይት መውጣቱን የዲፕሎማት ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ሬውተርስ ዘግቧል።
ይሄን ተከትሎ በሱዳን ለ6 ሳምንታት የቀጠለው ውጊያ በግጭት ማቆም ስምምነት ሊገታ ይችላል በሚል የተያዘው ተስፋ ወደ ቀቢጸ ተስፋ መቀየሩን ነው ዘገባው ያመለከተው።
የሱዳን ተፈላሚ ኃይሎች ከዚህ ቀደም የደረሱትን ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም ስምምነት ለ 5 ቀናት ለማራዘም ተስማምተናል ሲሉ ትናንት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
🇸🇸#ደቡብ ሱዳን
የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ ተጥሎ የነበረውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ለ 1 አመት ማራዘሙን አስታወቀ፡፡
ምክር ቤቱ ማዕቀቡን ለአንድ አመት ሲያራዝም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው ቻይና እና ሩሲያ ድምፅ ተአቅቦ ማድረጋቸው ነው የተነገረው።
ደቡብ ሱዳን እና የምክር ቤቱ ተለዋጭ አባላት የሆኑት 3 የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔን ተቃውመዋል መባሉን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
🇩🇪#ጀርመን
ሩሲያ በጀርመን ያሉ 4 የቆንስላ ፅህፈት ቤቶቿን እንድትዘጋ በጀርመን ታዘዘች ።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ክሪስቶፈር በርገር ጀርመን በሩሲያ ያሏትን የዲፕሎማቶች ቁጥር እንድትቀንስ መደረጉን ተከትሎ በጀርመን ያሉ 4 የሩሲያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲዘጉ የሀገሪቱ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ አስተዳደር ወስኗል ብለዋል።
የሀገራቱ አዲሱ ውዝግብ የጀርመን እና የሩሲያ ግንኙነት እጅግ የተቀዛቀዘ ደረጃ ላይ መድረሱን ማሳያ ነው ሲል አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
🇰🇵#ሰሜን ኮሪያ
ሰሜን ኮሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመጠቀችው የስለላ ሳተላይት ባጋጠመው እክል ባሕር ውስጥ ተከስክሶ መውደቁ ተሰማ።
ሰሜን ኮሪያ በቀጣናው ያሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማትን ለመሰለል በሚል ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ህዋ ያመጠቀችውን ሳተላይት ያስወነጨፈው ሮኬት ሞተሩ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ሳቢያ ሳተላይቷ በቢጫ ባሕር ተከስክሳ መውደቋ ነው የተነገረው፡፡
ሰሜን ኮሪያ ጠላት ስትል የፈረጀቻቸውን አሜሪካ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያን ለመሰለል በሚል የወታደራዊ ቅኝት ሳተላይት ልታመጥቅ እቅድ መያዟን ከወራት በፊት ይፋ ማድረጓ ይታወሳል