News

አዲስ ነገር – የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤጀንሲ በአውሮፓ ትልቁ የሆነው በዩክሬን የሚገኘው የዛፓሮዢያ የኒውክለር ጣቢያ ደህንነት ጉዳይ አሳስቦኛል አለ።

🇺🇦#ዩክሬን :
የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤጀንሲ በአውሮፓ ትልቁ የሆነው በዩክሬን የሚገኘው የዛፓሮዢያ የኒውክለር ጣቢያ ደህንነት ጉዳይ አሳስቦኛል አለ።
የሩሲያ አስተዳዳሪዎች ከዛፓሮዢያ የኒውክለር ጣቢያ አካባቢ ካሉ ከተሞች የሚኖሩ ዜጐቻቸውን እና ወታደሮቻቸውን ለቀው እንዲወጡ ማድረጋቸውን ተከትሎ የዩክሬን ኃይሎች በአቅራቢያው በከፈቱት ጥቃት የዛፓሮዢያ የኒውክለር ጣቢያ አደጋ ውስጥ መሆኑን ነው የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤጀንሲ ይፋ ያደረገው ::
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ በዛፓሮዢያ የኒውክለር ጣቢያ አቅራቢያ በቀጠለው ግጭት ግዙፉ የኒውክለር ጣቢያ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን ነው ያስታወቁት።
ዘገባው የአሶሺየትድ ፕሬስ ነው፡፡
🇸🇾#ሶሪያ
የአረብ ሊግ ላለፉት 12 አመታት አግዷት የነበረችውን ሶሪያ በድጋሚ የሊጉ አባል አገር አድርጐ መቀበሉን አስታወቀ።
በግብፅ መዲና ካይሮ የመከሩት የአረብ ሊግ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በእግድ ላይ የቆየችውን ሶሪያን ዳግም የሊጉ አባል አድርገው መቀበላቸውን የአረብ ሊግ ቃለ አቀባይ ጋማል ሮሺ ናቸው ያስታወቁት ።
ሶሪያ ከበርካታ የአረብ ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን እያሻሻለች ወምጣቷ ሲነገር ኳታር የሶሪያ ጦርነት ፖለቲካዊ እልባት ሳያገኝ ከሶሪያ ጋር ግንኙነቴን አላድስም ማለቷ ተሰምቷል፡፡
ዘገባው የፒቢኤስ ኒውስ ነው፡፡
🇸🇸#ደቡብ ሱዳን
ደቡብ ሱዳን በሱዳን በቀጠለው ግጭት ሳቢያ በሀገሪቱ በኩል የምትልከው የነዳጅ ዘይት ምርት እንዳይቆም መስጋቷ ተሰምቷል ።
የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ከደቡብ ሱዳን ተነስቶ ፖርት ሱዳን ድረስ የሚዘልቀው የደቡብ ሱዳን የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር በሱዳን በቀጠለው ግጭት ምክንያት ሊወድም ይችላል በሚል መስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ሱዳን መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሱዳን ተባብሶ በቀጠለው ግጭት ሳቢያ በደቡብ ሱዳን የነዳጅ ማውጫ ጉድጓዶች የሚሰሩ ኩባንያዎች እና ሰራተኞቻቸው ጭምር ሥራ ለማቆም እየተገደዱ መሆኑ አስጊ ነው ብለዋል።
ደቡብ ሱዳን 90 በመቶ የነዳጅ ምርቷን በሱዳን በኩል የምትልክ መሆኑ ሲነገር የጁባ መንግስት ለሱዳን በአውሮፓውያኑ 2022 ብቻ 148 ሚሊዮን ዶላር የአገልግሎት ክፍያ ፈጽሟል፡፡
በተያያዘ መረጃ ደቡብ ሱዳን የምግብ ምርቶቿን በሱዳን በኩል የምታስገባ ከመሆኑ አንጻር የሱዳን ግጭት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ደቡብ ሱዳን ለከፋ የምግብ እጦት ልታጋለጥ ትችላለች ተብሏል።
ዘገባው የዘ ኢስት አፍሪካን ነው።
🇨🇬#ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በደረሰ የጎርፍ አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 4ዐዐ መድረሱን የሀገሪቱ መንግስት አስታወቀ።
በሀገሪቱ ካሌዌ በተባለው ግዛት ሳውዝ ኪቩ አካባቢ ከ 3 ቀናት በፊት ባጋጠመው የጎርፍ አደጋ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር በትንሹ 394 መድረሱን ነው አንድ ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለሥልጣን ለኤኤፍ ፒ የገለፁት ።
በጎርፍ አደጋው ምክንያት የመሬት መንሸራተት እና የመስጠም አደጋዎች ደርሰዋል ተብሏል፡፡
ዘገባው የፒቢኤስ ኒውስ ነው፡፡
ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ

👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)

👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00

ዘወትር ቅዳሜ

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ዜናዎች በፍጥነት እና በየእለቱ ይዘገቡበታል።

አዲስ ነገር / What’s New