Sports

ኢትዮጵያዊ አትሌቶች በ18ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ኢትዮጵያዊ አትሌቶች በ18ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አስደናቂ ወጤት ማስመዘገባቸውን ቀጥለዋል። ሰኞ በተደረጉት ተጠባቂ የፍጻሜ ውድድሮች በሴቶች የማራቶን ውድድር ጎተይቶም ገ/ሥላሴ የአለም ሻምፒዮናውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር አሽናፊ ስትሆን በ3ሺ የወንዶች መሰናክል ለሜቻ ግርማ የብር ሜዳልያ አግኝቷል። አስደናቂ ፉክክር በታየበት የ1500 ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ደግሞ ጉዳፍ ጸጋዬ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳልያ ባለቤት ሆናለች።

ከሰባት አመታት መልስ በአለም ሻምፒዮናው በማራቶን ውድድር የወርቅ ሜዳልያ ለሀገሯ ያስገኘችው ጎተይቶም ገ/ስላሴ ከድሏ መልስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራት ቆይታ ደስ ብሎኛል ደስታዬ ግን የተዘበራረቀ ነው ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደተደሰተው የእኔ እናት እና አባትም ሲደሰቱ ብሰማና ባያቸው ደስ ይለኝ ነበር ። ያለች ሲሆን በመጀመርያ እግዚአብሔር ነው የረዳኝ ፣ ከዚያም በማሰልጠን ብቻ ሳይሆን እንደ ወንድም ሆነው እንዳይከፋኝ እያገዙ ለዚህ ያበቁኝ አሰልጣኞቼ ናቸው፡፡ አይዞሽ ሁሉም ያልፋል እያሉ እዚህ ያደረሱኝ በማለት ለቡድን አጋሮቿ ጎተይቶም ገ/ሥላሴ ከአስደናቂው የማራቶን ድሏ መልስ ምስጋናዋን አድርሳለች።

በ3ሺ ሜትር የወንዶች መሰናክል ውድድር ውጤታማ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው እና በአለም ሻምፒዮናውም የብር ሜዳልያ ያሸነፈው ለሜቻ ግርማ “በበኩሉ ውድድሩ በጊዜ ባለመቆረጡ እና እስከ መጨረሻው በዛ ብለን በመምጣታችን ምክንያት ላለመጠላለፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረብን ። ምንም እንኳን ራሴን ወደ ወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊነት መለወጥ እንዳለብኝ ባስብም ባገኘሁት የብር ሜዳሊያ ግን በጣም ደስተኛ ነኝ ” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል ።

ሁለተኛ የአለም ሻምፒዮና የብር ሜዳልያዋን በ1500 ሜትር በሂውጅን ያሳካችው ጉዳፍ ጸጋዬም ከውድድሩ መልስ ይህንን ብላለች፡፡ “ጠብቀነው የነበረው ስሜቱም ወርቅ ነበር ፣ ሀገራችንም የምትፈልገው እሱን ነው የቻልነውን ነገር አድርገን ተሸንፈናል ውጤቱን በፀጋ መቀበል ነው ፣ በውጤቱም ደስተኛ ነኝ ስትል ተደምጣለች። አትሌቷ አክላም በነበረው የንፋስ ሁኔታ ራሴ መርቼ የብር ሜዳሊያ በማግኜቴ ደስታ ተስምቶኛል” ስትል በአለም ሻምፒዮናው የብር ሜዳልያ ማግኘቷ የተለየ ስሜትን እንደሰጣት ገልጻለች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለም የ1500 ሜትር የወንዶች የፍጻሜ ውድድር ዛሬ ለሊት ላይ ይደረጋል ፡፡

ኢትዮጵያ በታደሰ ለሚ አማካኝነት የምትወከልበት መድረክም 11፡30 ሲል በሂውጅን ይከወናል፡፡ ሳሙኤል አባተ እና ሳሙኤል ተፈራ ከማጣሪያው ቀድመው በተሰናበቱበት ውድድር ለመጨረሻው ምዕራፍ የበቃው ታደሰ ለሚ ለሀገሩ ተጨማሪ ሜዳልያዎችን ለማስመዝገብ ወሳኙን ውድድር ያደርጋል፡፡ በቤልግሬድ በተደረገው የቤት ውስጥ ሻምፒዮና 4ኛ ደረጃን የያዘው አትሌቱ በቅርቡ ውድድር ባደረገባቸው 10 የ1500 ሜትር የውድድር ድግሶች 4ቱን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ችሏል፡፡
ሪፖርተር፡ ፈይሰል ዛኪር

የኢቢኤስ የአዲስ ነገር / What’s New መረጃዎችን በሚከተሉት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ይከታተሉ::

ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ

👉 የማለዳ ዜና ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት እስከ 2:00 / በድጋሚ ከ ጠዋቱ 3፡00 እስከ 3፡30

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:30 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት (በቀጥታ)

👉 የምሽት ዜና ከምሽቱ 1:30 እስከ 2:00

ዘወትር ቅዳሜ

👉 የእኩለ ቀን ዜና ከቀኑ 7:00 ሰዓት እስከ 8:00 ሰዓት

አዲስ ነገር / What’s New

EBSTV WRLDWIDE

EBSTV WRLDWIDE

EBS