ዓለም እየተጋፈጠቻቸው ለምትገኛቸው ችግሮች ፈጠራ የታከለባቸው ምላሾች አስፈላጊ ናቸው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዓለም እየተጋፈጠቻቸው ለምትገኛቸው ችግሮች ፈጠራ የታከለባቸው ምላሾች አስፈላጊ ናቸው ሲሉ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የገንዘብ፣ እቅድ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች 53ኛ ጉባዔ ላይ በተሳተፉበት ወቅት ነው፡፡
በመክፈቻ ንግግራቸው ዓለማችን እየተጋፈጠች ከምትገኛቸው ተፈጥሯዊ እና ሰብዓዊ ነውጦች ጋር ተያይዞ፣ ፈጠራ የታከለባቸው ምላሾች አስፈላጊ መሆናቸው የአጀንዳውን ወቅታዊነት እንደሚያሳይም ገልጸዋል፡፡
አፍሪካ የኮቪድ19ኝን ቀውስ በመጋፈጥ ሂደት ውስጥ የመቋቋም ችሎታዋን ከማሳየት ባለፈ መፍትሄዎችን ለመቅረፅ እና ተግባራዊ ለማድረግ ያሳየችውን አቅም እና ዝግጁነት አድንቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣይ አቅጣጫዎች በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በአየር ንብረት ለውጥ ተኮር ኢኮኖሚ እና ተቋማዊ ማዕቀፎችን ለትግበራ በሚያመች መንገድ ማብቃት ላይ ማተኮራቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል::