News

የአሉቶ ላንጋኖ የከርሰ ምድር እንፋሎት የማስፋፊያ ፕሮጀክት የምርት ሙከራ ጀመረ

ከአዕንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ታስቦ እየተሰራ ያለው የአሉቶ ላንጋኖ የከርሰ ምድር እንፋሎት ማስፋፊያ ፕሮጀክት በአንደኛው ጉድጓድ የምርት ሙከራ በይፋ መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡

አሁን ተጠናቆ የሙከራ ስራ መጀመሩ የተነገረለት አንደኛው ጉድጓድ በአሉቶ የከርሰ ምድር እንፋሎት ፍለጋ ቁፋሮ ከተጠናቀቀባቸው አራት ጉድጓዶች መካከል አንደኛው መሆኑን ያስታወቁት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ መሳይ ፍቃዱ የምርት ሙከራ በይፋ መጀመሩን በመጥቀስ የአምስተኛው ጉድጓድ ቁፋሮ ሰባት መቶ ሜትር ላይ መድረሱንም ጠቅሰዋል፡፡

ግንቦት 21 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው ፕሮጀክቱ ስድስተኛ ጉድጓድ የመቆፈር ስራ እንደሚሰራ የተጠቆመ ሲሆን የእንፋሎት ፍለጋ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማስጀመር ሪግ የተባለውን የመቆፈሪያ ማሽን ወደሚቆፈረው ቦታ አንቀሳቅሶ የመትከል ሥራ እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡

የእንፋሎት ፍለጋን ወደ ከርሰ ምድር እስከ 3 ሺህ ሜትር ጥልቀት እንደሚቆፈር የተናገሩት ባለሙያዎቹ አንድ ጉድጓድ ለመቆፈር በአማካይ እስከ 75 ቀናት ይፈጃል ያሉ ሲሆን ቁፋሯቸው ከተጠናቀቁት አራት ጉድጓዶች መካከል ሁለተኛው ጉድጓድ ከሁለት ሳምንታት በኋላ የሙከራ ሥራ እንደሚጀምርና በአጠቃላይ ከፕሮጀክቱ እስከ 70 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት መታሰቡን ተናግረዋል ፡፡
መረጃው የኢትዮጵ ኤሌክትሪክ ሃይል ነው፡፡