EthiopiaNews

የአየር መንገድ የትኬት ዋጋ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ቲኬት ላይ ምንም አይነት የተለየ የዋጋ ጭማሪ አለማድረጉን ተናግሯል።

የውጭ ምንዛሪ አተማመን ለውጥ ጋር በተያያዘ በዓለም-አቀፍ እና በሀገር ውስጥ ጉዞ የአውሮኘላን የትኬት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል በሚል የሚናፈሰው መረጃ ሀሰት ነው ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክትዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት አሠራር የዓለም-አቀፍ ጉዞ የአውሮኘላን ቲኬት ዋጋ የሚተመነው በአሜሪካን ዶላር ወይም ሌሎች ምንዛሪዎች ነው ያለው መረጃው የቲኬቱ ዋጋ የሚወሰነው ቲኬቱን በሚገዙበት ቀን የሀገሩ ገንዘብ ባለው የዶላር የውጭ ምንዛሬ ተመን መሰረት ተሰልቶ እንደሚሆን ገልጿል።

የዓለምአቀፍ በረራ ትኬቶች በአገር ውስጥ ሲገዙ ዋጋ የሚጨመረው ከወቅታዊው የብርና ዶላር ምንዛሪ አንፃር መሆኑን ገልጾ ደንበኞች ይህን እንዲረዱ ጠይቋል።
የሀገር ውስጥ በረራ የቲኬት ዋጋን በተመለከተ ምንም አይነት ለውጥ አላደረኩም ያለው አየር መንገዱ ወደፊት በጥናት በተደገፈ መልኩ መጠነኛ ማስተካከያ ሊያደረግ እንደሚችል ግንዛቤ እንዲወሰድ ሲል ከወዲሁ አስታውቋል።