LatestNews

የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰሜኑ የኢትዮጵያ አካባቢ እየቀረበ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ጎበኙ::

 የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ የብሪታኒያ ተራድኦ ድርጅት በሰሜኑ የኢትዮጵያ አካባቢ እያቀረበ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ጎበኙ፡፡

ሚኒስትሩ ጎንደር በመገኘት የብሪታኒያ ተራድኦ ድርጅት ለዓለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም እና በተመድ የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች አስተባባሪ ቢሮ ያደረገውን የ10 ሚሊየን ፓውንድ የሰብዓዊ ድጋፍ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ሰብዓዊ ድጋፉ በተፈለገው ቦታ ተደራሽ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል፡፡

ዶሚኒክ ራብ በኬንያና ሱዳን ሲያደርጉት የነበረውን ጉብኝት አጠናቀው ትናንት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይታወሳል፡፡

ሚኒስትሩ ትናንት ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በማጠናከር፣ ቀጠናዊ ጉዳዮች እና በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እና የመሰረተ ልማት አውታሮችን መልሶ መገንባት ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል፡፡

ሚኒስትሩ እንግሊዝ በትምህርት ዘርፉ ድጋፍ ከምታደርግባቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በሆነው በምስራቅ ጮራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው ጉብኝት አድርገዋል።