EthiopiaNews

የዓለም አቀፍ የሰው አዘዋዋሪው

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲፈለግ የነበረውን አደገኛ የሰው አዘዋዋሪ ይትባረክ ዳዊት አለሙን በትግራይ ክልል፣ ሽረ ከተማ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አሳውቋል።

ይትባረክ ዳዊት አለሙ ቤተሰቦቹ በልጅነቱ ያወጡለት ስም ጳውሎስ ዳዊት ወልዳይ ሲሆን ወንጀል መስራት ሲጀምር የሚታወቅባቸው ስሞች አድሀኖም ሱዳን፣ አህመድ ሱማሊያ ጅቡቲ እና ኬንያ የሚጠቀምበት ስም ሙኒር ነው። ክብሮም ደግሞ በስዊድን እና በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የሚጠቀምባቸው ሀሰተኛ ስሞች ናቸው።

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው ፤ በምስራቅ አፍሪካ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከሚሰራ በምህፃሩ ሮክ “ROCK ” ከተሰኘ ድርጅት ጋር በተደረገ የመረጃ ልውውጥ ነው።

ፖሊስ ከይትባረክ ዳዊት (ክብሮም) በተጨማሪ ሌሎች 9 ግብረአበሮቹም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና የተጠርጣሪዎቹን የባንክ ሂሳብና ንብረት በፍርድ ቤት እንዲታገድ ማድረጉን አሳውቋል።

ተጠርጣሪውና 9 ግብረ-አበሮቹ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ከኢትዮጵያ፣ከሱዳን፣ከኤርትራ፣ ከጅቡቲ፣ ከኬንያ እና ከሶማሊያ ወጣቶችን በመመልመል ለከፍተኛ ስቃይ ዳርገዋል ተብሏል።

እነዚሁ ተጠርጣሪዎች ተጎጂዎችን ሊቢያ ውስጥ ባዘጋጇቸው 5 መጋዘኖች በማገት ቤተሰቦቻቸውን ገንዘብ ይጠይቁ ነበር።

ይትባረክ ከግብረአበሮቹ ጋር ፦ከ3,000 በላይ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወሩ፣ ከ100 በላይ ሰዎች ለሞት እንዲዳረጉ ማደረጉ፣ ከ50 በላይ ሴቶች እንዲደፈሩ ማድረጉ ተገልጿል።

ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ሲንቀሳቀስ ነበር።

ፖሊስ ከ100 በላይ ተጎጂዎችንና ቤተሰቦቻቸውን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምስክርነት ቃል የመቀበል ሥራ መስራቱን ገልጿል፡፡

ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሊቢያ፣ ሱዳን፣ ቤልጂየም፣ እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ፣ ኔዘርላንድ፣ ሉግዘንበርግ እና ስዊዘርላንድ ከሚገኙ 16 ተጎጂዎች ላይ ቃል መቀበሉንም አመልክቷል።

አሁን ላይ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ ለዓቃቤ ሕግ መላኩን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አሳውቋል።

መረጃው ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘ ነው።

#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN