የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሞት በኋላ የዓይን ብሌን ለመለገስ የሚያስችል ሃይማኖታዊ ውሳኔ ወይንም (ፈትዋ) መስጠቱን ዛሬ በይፋ አስታውቋል።
ውሳኔው የተላለፈው የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ጥቅምት 7 ቀን 2019 ዓ.ም በጉዳዩ ላይ ሃይማኖታዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ለምክር ቤቱ የዑለማ ጉባኤ ከፍተኛ የፈትዋ ኮሚቴ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ነው።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ጸሐፊ ሃጂ መሱድ አደም እንደገለጹት፣ ኮሚቴው የሸሪዓን መሠረታዊ ዓላማዎች መነሻ በማድረግ ጥልቅ ጥናትና ምርምር ካካሄደ በኋላ፣ ጥቅምት 25 ቀን ባደረገው ስብሰባ ልገሳው እንዲፈቀድ ወስኗል።
የምክር ቤቱ የዑለማ ጉባኤ ጸሐፊ ሼህ መሀመድ ዘይኑ የዓይን ብሌን ልገሳው ተግባራዊ የሚደረግባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በዝርዝር አብራርተዋል፡፡
በዚህም የለጋሹ ሕይወት ማለፉ በሕክምና ባለሙያዎች በእርግጠኝነት ሲረጋገጥ፤ ለጋሹ ከመሞቱ በፊት በፈቃደኝነት ኑዛዜ ካደረገ፤ ልገሳው ያለምንም የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ ክፍያ በበጎ ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሠረተ ሲሆን፤ እንዲሁም ብሌኑ የዓይን ብርሃን ለሚያስፈልገው ሰው ተጨባጭ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑ በባለሙያ ሲረጋገጥ ነው ተብሏል።
